“ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤቴ ናት”ቢያትሪስ ቺቤት

0
25

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለሚካሄደው በባንክ ኦፍ አሜሪካ የቀረበው ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎሜትር ውድድር የክብር እንግዳ ኾና የመጣችው ኬንያዊቷ ኮከብ አትሌት ቢያትሪስ ቺቤት፣ የኢትዮጵያን ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ስትረግጥ የተሰማትን ስሜት የገለጸችው «ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤቴ ናት» በሚል ፍቅርና አክብሮት የተሞላበት ቃል ነው።

በዓለም አትሌቲክስ መድረክ ላይ ኢትዮጵያ እና ኬንያ በመሙ ላይ እስከ መጨረሻዋ ሴኮንድ የሚፋለሙ ተቀናቃኞች ቢኾኑም፣ ከመሮጫው ትራክ ውጪ ግን አንዱ የሌላውን ቤት እንደራሱ የሚቆጥር ጥልቅ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እንዳላቸው የቺቤት መገኘት ሕያው ምስክር ኾኗል።

ከታላቁ ሻምፒዮን ኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር ለመቀራረብ እና ለመተዋወቅ መጓጓቷን ስትገልጽ የነበረው ኩራት፣ የሁለቱን ሀገራት የአትሌቲክስ ትስስር ከውድድር ባለፈ የጋራ ታሪክ እና ክብር መገለጫ አድርጎታል።

የቢያትሪስ ቺቤት ስም ሲነሳ በቅርብ ዓመታት በዓለም አትሌቲክስ ላይ ያሳረፈችው ደማቅ አሻራ አብሮ ይታወሳል። እ.ኤ.አ. 2024 እና 2025 ለእሷ የስኬት ማማ ላይ የወጣችባቸው ወርቃማ ዓመታት ነበሩ።

በ10,000 ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን ለመስበር አቅዳ በትጋት በመሥራት ታሪክ ስትጽፍ፣ በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና መድረኮች ላይም የበላይነቷን በማረጋገጥ የዘመኑ የረጅም ርቀት ንግሥት መኾኗን አስመስክራለች።

ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ ድካም እና ታላላቅ ድሎች በኋላ ወደ 2026 ስትመለስ ሕይወት ሌላ ምዕራፍ አምጥቶላታል።

የወንድ ልጅ እናት ከኾነች በኋላ የእናትነትን ኀላፊነት ከፕሮፌሽናል አትሌቲክስ ሕይወት ጋር ማመጣጠን ግድ በኾነበት በዚህ ወቅት፣ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች አለመኖራቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰውነቷ እንዲያገግም እረፍት መርጣለች።

ከእረፍት መልስ ዛሬ ከዜሮ ጀምራ ራሷን እያዘጋጀች ያለችው ይህች ሻምፒዮን፣ ዐይኗን ያሳረፈችው በ2028 በሎስ አንጀለስ በሚካሄደው ኦሎምፒክ ላይ ዳግም ጠንካራ ኾና በመቅረብ ታሪክን ለመድገም ነው።

ይህ የቺቤት የአልሸነፍ ባይነት መንፈስ እና የማያቋርጥ ጥረት፣ ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በመድረኩ ላይ ካስተላለፈው ጥልቅ መልዕክት ጋር በቀጥታ ይተሳሰራል።

ኃይሌ «ኬንያውያን አትሌቶች ባይኖሩ እኛ ኢትዮጵያውያን የዛሬውን ያህል ጠንካራ አንኾንም ነበር፤ እኛም ለኬንያ አስፈላጊዎች ነን» ሲል የተናገረው ሃሳብ የምሥራቅ አፍሪካን የረጅም ርቀት የበላይነት ሚስጥር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ለረጅም ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ እና የኬንያ ፉክክር አንዱ ሌላውን ለማሸነፍ ሲል የሚደረጉት ፉክክሮች ክብረ ወሰኖችን እንዲሰበሩ አስገድዷል።

ውድድሩ ካለቀ በኋላም መከባበርን በመተቃቀፍ የገለጹባቸው ወቅቶች እንዲሁ ብዙዎች ናቸው።

በቺቤት 2024 እና 2025 ድሎች ውስጥ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብርቱ ፉክክር እንደነበረ ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያን ጀግኖችም በዓለም አደባባይ ሲነግሡ ኬንያውያን ተቀናቃኞቻቸው የስኬታቸው መሠረት ኾነው ቆይተዋል።

በአጠቃላይ በታላቁ ሩጫ መድረክ ላይ የታየው የቢያትሪስ ቺቤት እና የኃይሌ ገብረሥላሴ መገናኘት፣ በአትሌቲክስ ዓለም ውስጥ ያለውን ጤናማ ፉክክር ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያደረሰ ክስተት ነው።

አንዷ ከወሊድ በኋላ ለሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ ከዜሮ እየተነሳች ባለችበት፣ ሌላው ደግሞ የትናንትናውን ታሪክ እያስታወሰ ለነገው ትውልድ መንገድ በሚያሳይበት በዚህ መድረክ ላይ፣ የኢትዮጵያ እና የኬንያ የአልሸነፍ ባይነት ጉዞ አንዱ ያለ ሌላው የማይታሰብ የጋራ ድል መኾኑ ዳግም ያረጋገጠ ነው።

ለዚህም ነው ሁለቱ ሀገራት አንዳቸው ያለአንዳቸው ፉክክር እዚህም እንዳማይደርሱ የሚያቁት።

ለቺቤት ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤቷ ለመኾኗ ያክል ለኃይሌም ፓል ቴርጋትን የመሰሉ ወዳጆችን ያፈራበት ሁለተኛ ቤቱ ናት የምንለው።

#ሐናማርያም_መስፍን

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_12_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here