አርሰናል ከኒውካስል ዩናይትድ ተጠባቂ ጨዋታ

0
47

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት፣ የሊጉ መሪ አርሰናል ዛሬ ምሽት 2፡30 ወደ ሴንት ጄምስ ፓርክ አቅንቶ ኒውካስል ዩናይትድን ይገጥማል።

በ27 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን በአምስት ነጥብ ልዩነት እየመራ የሚገኘው አርሰናል፣ ተከታታይ ስድስተኛ የሊግ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል።

መድፈኞቹ በሊጉ ባደረጓቸው ያለፉት አራት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳይቆጠርባቸው በድምሩ 5 ለ 0 አሸንፈዋል፤ ይህንንም ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርባቸው ካሸነፉ ከ1987 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች መረባቸውን ሳያስደፍሩ ድል ያደርጋሉ።

በተጨማሪም አርሰናል በመጀመሪያዎቹ 11 ጨዋታዎች 10 ድል ያስመዘገበ አምስተኛው የፕሪሚየር ሊግ ቡድን ለመሆን የሚፋለም ሲሆን፣ ድሉ ለአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ 159ኛ የፕሪሚየር ሊግ ድላቸውን በማስገኘት በሊጉ ታሪክ 10ኛው ከፍተኛ አሸናፊ አሰልጣኝ ያደርጋቸዋል።

በአንጻሩ በ12 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኒውካስል ዩናይትድ፣ ካለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በሁለቱ ብቻ ነው።

በ2026 በሜዳቸው ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በመሸነፍ ከሁሉም ቡድኖች የከፋ ሪከርድ ያላቸው ማግፓይሶቹ፣ በሴንት ጄምስ ፓርክ ባደረጓቸው ያለፉት ሁለት ጨዋታዎችም በአስቶን ቪላ እና በኤቨርተን በተመሳሳይ 1 ለ 0 ተሸንፈዋል።

በዚህም ምክንያት በአሰልጣኛቸው ማቲያስ ያይስለ ላይ ጫናው የበረታ ሲሆን፣ ባለፈው ጨዋታም ከፉልሃም ጋር 80ኛው ደቂቃ ላይ የመሩበትን ውጤት ማስጠበቅ ተስኗቸው 1 ለ 1 ተለያይተዋል።

በእርስ በርስ ግንኙነት አርሰናል ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ሲወስድ፣ ኒውካስልን በፕሪሚየር ሊጉ 38 ጊዜ አሸንፏል።

ኒውካስል ከሊጉ መሪዎች ጋር ባደረጋቸው ያለፉት 18 የሊግ ጨዋታዎች እንዲሁም ከወቅቱ ሻምፒዮኖች ጋር ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች አንድም ድል አላስመዘገበም።

አርሰናል ቡካዮ ሳካን በጉዳት እንዲሁም ማክስ ዶውማንን በቅጣት የማያሰልፍ ሲሆን ማርቲን ዙቢሜንዲም የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

በኒውካስል በኩል ኒኮ ጎንዛሌዝ እና ጆ ዊሎክ ለጨዋታው ይደርሳሉ ተብሎ ቢጠበቅም ጆሊንተን እና ኢወን ጃኡን ከስብስቡ ውጭ ናቸው።

በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ በ22 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ፣ ዛሬ ቀን 9፡30 በኢቲሃድ ስታዲየም ፉልሃምን ያስተናግዳል።

በአሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ የሚመራው ሲቲ ከአርሰናል ጋር ያለውን የስድስት ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ባለፉት ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ያጋጠመውን ተከታታይ ሽንፈት ለማቆም፣ ባለፉት 10 የእርስ በርስ ግንኙነቶች ያሸነፈውን እና በ10 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ፉልሃምን ይገጥማል።

በሌሎች ጨዋታዎች ምሽት 12፡00 ቦርንማውዝ ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ አስቶን ቪላ ከሰንደርላንድ፣ ቼልሲ ከሊድስ ዩናይትድ፣ ኮቨንትሪ ሲቲ ከክሪስታል ፓላስ እንዲሁም ቶተንሃም ከኢፕስዊች ታውን በተመሳሳይ ሰዓት ይጫወታሉ።

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_12_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here