ታሪካዊው የ61 ሺህ ተሳታፊዎች ክብረወሰን እና የ500 ሺህ ብር ሽልማት በታላቁ ሩጫ!

0
49

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተሳታፊዎች ቁጥር አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።

ዘንድሮ አጠቃላይ የተመዝጋቢዎች ቁጥር 61 ሺህ በመድረስ አዲስ ሪከርድ የተመዘገበ ሲኾን የውድድሩ አሸናፊዎችም እስከ 500 ሺህ ብር የሚጠጋ ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል።

‎የውድድሩ መስራች ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ እና የኦፕሬሽን ማናጀሩ ዳግም ተሾመ የዘንድሮውን ዝግጅት እና የቀጣይ ዓመት ታላላቅ ዕቅዶችን አስመልክቶ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

‎የተሳታፊዎች ቁጥር 61 ሺህ መድረሱ ታላቅ ስኬት መኾኑን የገለጹት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ለአሸናፊ አትሌቶች የሚሰጠው ሽልማትም ወደ 500 ሺህ ብር መደረሱን ጠቁመዋል።

‎ከማኅበራዊ ኀላፊነት እና ዓለም አቀፍ አጋርነት አንጻር ደግሞ ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር በመተባበር በትምህርት፣ በሕጻናት ሥነ-ጽሑፍ፣ በአቅም ግንባታ እና በገቢ ማሠባሠብ ዘርፎች በጋራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

በዚህ የገቢ ማሠባሠቢያ መርሐ ግብርም ወደ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

‎በቀጣይ ዓመት ተግባራዊ የሚደረጉ ለውጦችንም ይፋ አድርገዋል።

በዚህም መሰረት እያንዳንዱ ተወዳዳሪ ውድድሩን የጨረሰበትን ትክክለኛ ሰዓት ማወቅ እንዲችል የሚያስችል የታይም ቺፕስ (Time Chips) ቴክኖሎጂን በስፋት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ።

‎በተጨማሪም ለሁሉም ተሳታፊዎች አንድ ወጥ እና ደረጃውን የጠበቀ የመሮጫ ልብስ በቀጥታ በራሱ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሠርቶ የሚቀርብ ይኾናል።

‎የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኦፕሬሽን ማናጀር ዳግም ተሾመ በሰጠው ማብራሪያ የታላቁ ሩጫ ቤተሰብ ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር በጋራ መሥራቱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

‎የተሳታፊዎችን ቁጥር እና ፍላጎት መሠረት በማድረግ ውድድሩ ከሦሥት የተለያዩ ቦታዎች ይጀመራል ብለዋል።

‎ሩጫው ከመስቀል አደባባይ፣ ከጊዮን ሆቴል እና ሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት ይነሳል ነው ያሉት፡፡

ተሳታፊዎች በፈለጉት ሰዓት ርቀቱን አጠናቅቀው መጨረስ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯልም ተብሏል፡፡

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_11_2019_ዓ_ም

በሐናማርያም መስፍን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here