የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ላይ ዕምነት እንደሌለው ገለጸ።

0
77

 

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የዓለም ዋንጫን የንግድ ድርሻ ወይም “ፊፋ ፎርዋርድ ኢንተርፕራይዝ” በሚል አዲስ ዕቅድ ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ አቅደው እንደነበር ይታወሳል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን፣ የሰሜን፣ የመካከለኛው አሜሪካ እና የካሪቢያን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ዕቅዱን “በስውር የተጠነሰሰ እና ግልጽነት የጎደለው ስምምነት” ነው በማለት በዕቅዱ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ዕቅዱ ካልተሰረዘም የዓለም ዋንጫን ጨምሮ በማንኛውም የፊፋ ውድድሮች ላይ ላለመሳተፍ በአንድ ድምጽ ወስኖ እንደነበርም ቢቢሲ ዘግቧል።

ፊፋ ከቀረበበት ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ እና ከውስጥ የባለሥልጣናት መልቀቅ በኋላ የዓለም ዋንጫን ድርሻ የመሸጥ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለመሰረዝ ተገድዷል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ባወጣው መግለጫ ዕቅዱ ቢሰረዝም “የአሁኑ የፊፋ አመራር የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበርን ብቻ ሳይኾን የሌሎችን የእግር ኳስ ቤተሰቦች ዕምነት አጥቷል” በማለት ለጂያን ኢንፋንቲኖ የሚሰጠውን ድጋፍ ማንሳቱን አረጋግጧል።

እንደ ብሪታኒያው ዘ ቴሌግራፍ እና ጎል ዶት ኮም ዘገባ ደግሞ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ኀላፊነታቸውን እንዲለቁ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ኢንፋንቲኖ በገዛ ፈቃዳቸው ኀላፊነታቸውን የማይለቁ ከኾነም የማኅበሩ 55 አባል ሀገራት እሱን ከሥልጣን ለማስወገድ የሚያስችል ድምጽ ለመስጠት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል።

ድምጽ መስጠቱን በይፋ ለመጀመር ከፊፋ 211 አባላት መካከል የ43 ሀገራት ድጋፍ ብቻ የሚያስፈልግ ሲኾን የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ይህንን በቀላሉ ማሠባሠብ እንደሚችል ገልጿል።

#Ameco #sport #Football #FIFA #CAF #UEFA

#ባሕር_ዳር #ሐምሌ_25_2018_ዓ_ም

በአድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here