የቀድሞ እግር ኳስ ኮከቦች እና ፍሬዎቻቸው በዓለም ዋንጫ

0
76

 

ባሕር ዳር: ሰኔ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በታላቁ እና ተወዳጁ የዓለም ዋንጫ መድረክ እንደ ተመልካች መታደም በራሱ ትልቅ ትውስታ እና የሕይዎት ስንቅ ነው፡፡ ሀገርን ከሚወክሉ 26 ተጫዋቾች መካከል መገኘት ደግሞ ትልቅ ስኬት እና ኩራትም ነው፡፡ በዚህ መድረክ ከዚህ ቀደም እንደ ቤተሰብ መታደል የኾነላቸው ለብሔራዊ ቡድን የተጠሩ ወንድማማቾችን አስታውሰን ነበር፡፡
ታዲያ በዚህ በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ጥምረት እየተከናወነ ባለው የዓለም ዋንጫ የቀድሞ ታላላቅ እግር ኳስ ኮከቦች ፍሬዎች የአባቶቻቸው ልጆች መኾናቸውን ለማስመስከር በታላቁ መድረክ በብሄራዊ ቡድኖች ሥብሥብ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ቦላቪአይፒ እና ኢ ኤስ ፒ ኤንን የመረጃ ምንጮች እንዳስነበቡት ከእነዚህ መካከል የተወሰኑት አባታቸው የወከለውን ብሄራዊ ቡድን አርማ ሲያስቀጥሉ ሌሎች የሌላ ብሄራዊ ቡድን ወክለው ተገኝተዋል፡፡
ከእነዚህ የአባት እና ልጅ የትውልድ ቅብብሎሾች መካከል ሁለቱ የፈረንሳይ 1998 የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ቡድን ሥብሥብ አባላት ፍሬዎች ናቸው፡፡

የ1998 የዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ ብራዚልን አሸንፋ ሻምፒዮን ስትኾን ሁለት ግብ ያሥቆጠረው ዜነዲን ዚዳን ነበር ፡፡ እርሱ በዓለም ዋንጫ በ1998፤ 2002፤ እና 2006 ተሳትፏል፡፡

አምሥት ግቦችንም አስቆጥሯል፡፡ አሁን ደግሞ ልጁ ሉካ ዚዳን በዓለም ዋንጫ ይገኛል፡፡ ሉካ ዚዳን የቤተሰቡ 2ኛ ልጅ ሲኾን በወጣት ብሄራዊ ቡድን ፈረንሳይን ቢያገለግልም ከ2025 ጀምሮ በዋና ብሄራዊ ቡድን ደረጃ ለአልጀሪያ በግብ ጠባቂነት ያገለግላል፡፡ አሁንም በዓለም ዋንጫ ከአርጀንቲና፤ ኦስትሪያ እና ዮርዳኖስ ጋር ለተደለደለችው አፍሪካዊት ሀገር አልጀሪያ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ ነው፡፡

ሌላው የ1998 የዓለም ዋንጫ የፈረንሳይ ስኬት አካል የነበረው ሊሊያም ቱራም ልጅ ማርከስ ቱራም በዓለም ዋንጫው ከፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ጋር ነው፡፡ አባቱ ሊሊያም ቱራም በዓለም ዋንጫ በ1998፣ 2002 እና 2006 ተሳትፏል፡፡

ዘንድሮ ከኢንተር ሚላን ጋር የሊግ ዋንጫን ያሳካው ማርከስ ቱራም ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበረው የ2002 የዓለም ዋንጫ ፈረንሳይን የወከለ ሲኾን አሁንም በታላቁ መድረክ የቡድኑ የአጥቂ አማራጭ ነው፡፡

የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ሃላንድ አባት አልፌ ሃላንድ በ1998 የዓለም ዋንጫ ኖርዌይን ወክሎ ተሳትፎ አድርጓል፡፡ የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ሃላንድም ሀገሩ ከ28 ዓመት በኋላ ለዓለም ዋንጫ እንድትበቃ ካስቻሉ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፤ አሁንም በዓለም ዋንጫው ጎልተው ከሚታዩ አጥቂዎች መካል አንዱ እንደሚኾን ሲጠበቅ እንደ አባቱ ሁሉ በዓለም ዋንጫ መሳተፉ እርግጥ ነው፡፡

የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድንም በትውልድ ቅብብሎሽ ተጠቃሚ ነው፡፡ ፓትሪክ ክላይቨርት በ1998 የዓለም ዋንጫ የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ተጨዋች ነበር፡፡ አሁን ልጁ ጀስቲን ክላይቨርት የኔዘርላንድ ብሄራዊ ቡድን የአጥቂ አማራጭ ነው፡፡

አሜሪካ የቀድሞ ኮከብ እግር ኳሰ ተጫዋች ልጆችን በቡድኗ አቅፋለች፡፡ የላይቤሪያዊው የቀድሞ ኮከብ እና የባሎንዶር አሸናፊ ጆርጅ ዊሃ ልጅ ቲሞቲ ዊሃ ለአሜሪካ ቡድን ከሁነኛ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡ አባቱ ጆርጅ ዊሃ ሀገሩ ላይቤርያን ለዓለም ዋንጫ ማብቃት ባይችልም ልጁ ግን ከአሜሪካ ጋር ተሳትፎ ላይ ነው፡፡

ሌላው አሜሪካዊ ጆቫኒ ሬና በአሜሪካ የመጀመሪያ ጨዋታ ግብ አስቆጥሯል፡፡ አባቱ ክላውዲዮ ሬና ደግሞ በአራት የዓለም ዋንጫዎች አሜሪካን ወክሏል፡፡
አርጀንቲና ሲሞኒ እና ፓዝ
የ2022 የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ አርጀንቲና የትውልድ ቅብብሎሽ መንገድ ላይ ናት፡፡

ከ1994 የዓለም ዋንጫ ጀምሮ ሦሥት የዓለም ዋንጫዎች ላይ ሀገሩን የወከለው የቀድሞው አማካኝ የአሁኑ የአትሌቲኮ ማድሪድ አሠልጣኝ ዲያጎ ሲሞኒ ልጅ ጆቫኒ ሲሞኒ አሁን በአርጀንቲና ሥብሥብ ውስጥ ነው፡፡ ሌላው አርጀንቲናዊ ፓብሎ ፓዝ በ1998 የዓለም ዋንጫ ሀገሩን ያገለገለ ሲኾን አሁን ደግሞ ወጣቱ ተጨዋች ኒኮ ፓዝ የአርጀንቲና ሥብሥብ አካል ነው፡፡

ፖርቹጋልም ቢኾን የትውልድ ቅብብሎሽ ተጠቃሚ ቡድን ነው፡፡ ሰርጂዎ ኮንሲሳዎ በ2002 የዓለም ዋንጫ ፖርቹጋልን ወክሎ ተጫውቷል፡፡ አሁን ደግሞ ልጁ ፍራንሲስኮ ኮንሲሳዎ የፖርቹጋል ቡድን አባል ነው፡፡

#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_የዓለም_ዋንጫ

በመለሰ ግዛቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here