ባሕር ዳር: ግንቦት 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አሠልጣኝ ማይክል ካሪክ የማንቸስተር ዩናይትድ ቋሚ አሠልጣኝ ኾነው ተሹመዋል።
ከአሠልጣኝ ሩበን አሞሪም ስንብት በኋላ ማንቸስተር ዩናይትን በጊዜያዊነት ተረክበው የቆዩት አሠልጣኝ ማይክል ካሪክ የማንቸስተር ዩናይትድ ቋሚ አሠልጣኝ ኾነው መሾማቸውን ክለቡ ይፋ አድርጓል።
ማይክል ካሪክ ማንቸስተር ዩናይትድን ከተረከቡ በኋላ ክለቡን ወደ አሸናፊነት መልሰውታል።
ከውጤት ቀውስ አውጥተው ክለቡ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሦሥተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ባሳዩት ድንቅ ሥራም የቋሚ አሠልጣኝነት ሹመት ተሰጥቷቸዋል።
ቢቢሲ በዘገባው ማይክል ካሪክ ማንቸስተር ዩናይትድን በጊዜያዊነት ከተረከቡ ጀምሮ በፕሪምየር ሊጉ እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ብዙ ነጥብ የሠበሠበ ክለብ የለም ብሏል።
ጊዜያዊ አሠልጣኝ ኾነው የቆዩት ማይክል ካሪክ በሜዳ ላይም ኾነ ከሜዳ ውጭ ባሳዩት ሥራ ተደንቀዋል ነው ያለው።
ማይክል ካሪክ በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት ለ12 ዓመታት በተጫዋችነት አሳልፈዋል። በክለቡ በነበራቸው ቆይታም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ጨምሮ በርካታ ዋንጫዎችን አሸንፈዋል።
በታርቆ ክንዴ
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት #ማንቸስተር_ዩናይትድ#
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !


