ባሕር ዳር፡ ግንቦት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሊቨርፑሉ ኮከብ መሐመድ ሳላህ በአሠልጣኝ አርነ ስሎት የጨዋታ ዘይቤ እና በክለቡ የአሁኑ የውድድር ዘመን ውድቀት ላይ በይፋ የሰነዘረው ትችት፣ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በሚገኘው አሠልጣኝ ላይ ያለውን ጫና አክብዶታል።
ሊቨርፑል በአስቶን ቪላ 4ለ2 ከተሸነፈ በኋላ ሳላህ በማኅበራዊ ሚዲያ ባጋራው ጽሑፍ ክለቡ የቀድሞው አሠልጣኝ ዩርገን ክሎፕ መለያ የነበረውን እና “ተጋጣሚዎች የሚፈሩትን የማጥቃት ማንነት” መልሶ ማግኘት እንዳለበት መግለጹን ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል።
ይህ የሳላህ ሀሳብ ከዚህ ቀደም በታኅሣሥ ወር ከሊድስ ዩናይትድ ጋር 3ለ3 ከተለያዩ በኋላ ካሳየው ቅሬታ የቀጠለ ሲኾን በአሠልጣኙ እና በተጫዋቹ መካከል ያለው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ መሻከሩን አመላካች ኾኗል።
አርነ ስሎት ሊቨርፑልን በተረከቡበት የመጀመሪያ የውድድር ዘመን የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ቢያነሱም በዘንድሮው የውድድር ዓመት ግን የክለቡ ዋንጫ የማግኘት ጉዞ በመክሸፉ እና ቡድኑ በተከታታይ ሽንፈቶች ውስጥ በመዘፈቁ በደጋፊዎች ዘንድ ያላቸው አመኔታ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መጥቷል።
የሊቨርፑል ደጋፊዎች የአርነ ስሎት ተተኪ አድርገው የሚመኙት የቀድሞ ተጫዋቻቸውን ዣቢ አሎንሶን ቢኾንም ስፔናዊው አሠልጣኝ ግን በሚቀጥሉት ቀናት የቼልሲ ዋና አሠልጣኝነትን ለመረከብ ከጫፍ መድረሱ ተገልጿል።
መሐመድ ሳላህ በሊቨርፑል ቤት የመጨረሻው የሚኾነውን ጨዋታ ከብሬንትፎርድ ጋር ያደርጋል።
በምስጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !



