ይህ ከእግር ኳስ ጨዋታ በላይ ነው!

0
35

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ይህ ተራ ግጥሚያ አይደለም፤ ይህ እግር ኳስ ብቻም አይደለም፤ ይህ ተዝናንቶ የሚለያዩበት ብቻ አይደለም፤ ይህ ክብር የሚገለጥበት፤ ታሪክ የሚመዘዝበት፤ የድል አድራጊነት ካባ የሚደረብበት፤ ከእግር ኳስ ባሻገር ያሉ የበላይነት ሀረጎች የሚመዘዙበት፤ ከሜዳ ባሻገር ያሉ ጉዳዮች የሚነሱበት ነው።

ሺዎች በስታዲየም፤ ሚሊዮኖች ከስታዲየም ውጭ በዓለም ዙሪያ በጉጉት ይጠብቁታል፤ ከእግር ኳስ ግጥሚያ በላይ ይመለከቱታል። በዚህ ግጥሚያ የሚገኝ ድል ከዋንጫ በላይ ያስደስታል፤ በዚህ ግጥሚያ የሚያጋጥም ሽንፈትም ዋንጫ ከማጣት በላይ ያበሳጫል፤ እንደ እግር እሳት ይለበልባል፤ ስለ ምን ቢሉ ይህ ከእግር ኳስ ባሻገር የክብር ሀረግ የሚመዘዝበት፤ የታሪክ ገጽ የሚገለጥበት፤ የበላይነት እና የበታችነት ጉዳይ የሚነሳበት ነውና።

የአንዲት ሀገር ኃያል ክለቦች፤ የዓለም የእግር ኳስ ከዋክብት መሰባሰቢያ ቤቶች፤ የምንግዜም ባላንጣዎች ኾነው ዓመታትን ተሻግረዋል ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና።

እነዚህ የስፔን ኃያላን ከስፔን ተሻግረው የዓለም ኃያላን የኾኑት ክለቦች ባላንጣነት የረጅም ዓመታት ታሪክ አለው። የእነዚህ ኃያላን ክለቦች ግጥሚያ ኤል ክላሲኮ እየተባለ ይጠራል።

አልጀዚራ የኤል ክላሲኮን ታሪክ ሲገልጽ በስፔን እግር ኳስ ታሪክ “ቪዬሆ ክላሲኮ” ወይም “አሮጌው ክላሲኮ” የሚል ገናና ታሪክ ያለው ስም ነበር። ይህ ስያሜ በሪያል ማድሪድ እና በአትሌቲክ ቢልባኦ መካከል የሚደረገውን ጨዋታ የሚያመለክት ነበር።

ባርሴሎና በስፔን እግር ኳስ ታሪክ ከሁለቱ ታላላቅ እግር ኳስ ክለቦች መካከል አንዱ ኾኖ ከመውጣቱ በፊት በሪያል ማድሪድ እና በአትሌቲክ ቢልባኦ መካከል የሚደረገው ግጥሚያ በስፔን እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በብዛት የተካሄደ ገናና ታሪክ ያለው ጨዋታ ነበር ይላል።

ኤል ክላሲኮ (El Clasico) የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በስፔን ጋዜጣ ላይ የታየው እ.አ.አ በ1960ዎቹ ውስጥ ነበር። ይህም በስፔን ውስጥ ባሉ ሁለት ታላላቅ እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎችን ለማመልከት የቀረበ ነበር ነው የሚለው አልጀዚራ።

አል ክላሲኮ ታሪካዊው ወይም ጥንታዊው ፍልሚያ የሚል ትርጓሜ ይሰጡታል። ይህ ፍልሚያ በእግር ኳስ ዓለም ውስጥ ካሉ እጅግ በጣም ጠንካራ እና ተቀናቃኝ የደርቢ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ተደርጎ ለረጅም ጊዜ ይታይ ነበር ይላል።

ኤል ክላሲኮ የሚለው ስያሜ አስቀድሞ የታወቀ ቢኾንም ስሙ ገናና እየኾነ የሄደው ግን እ.አ.አ በ1990ዎቹ ነው። በዚህ ዘመን በሪያል ማድሪድ እና በባርሴሎና መካከል ያለው ፉክክር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት የታወቀና ተወዳጅ ስያሜ መኾን ቻለ።

በወቅቱ በዮሃን ክራይፍ የሚመራው የባርሴሎና ቡድን በዓለም መድረክ የሚፈራ ኾነ። ነገር ግን ሪያል ማድሪድ ጠንካራ ፈተና እየደቀነባቸው ነበር። እግር ኳስ የበለጠ እየዘመነ፣ ከስፔን ውጭ ያሉ የእግር ኳስ ከዋክብት ወደ ስፔን ሲያመሩ ፍልሚያውም የበለጠ ከባድ ኾነ።

እንደ ዚነዲን ዚዳን፣ ሮናልዶ ናዛሪዮ እና ዴቪድ ቤካምን የመሳሰሉ ከዋክብትን መሰብሰብ የጀመረው ሪያል ማድሪድ የከዋክብት ስብስብ “ጋላክቲኮስ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጠው። ባርሴሎናም የከዋክብት መናኸሪያ ኾነ። በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለው ፍልሚያም ከባድ እና ገናና ኾነ። ጨዋታው እንደ ጨዋታ ብቻ ሳይኾን ክብር እና ታሪክ ተመዘዘበት። የጨዋታው ውጤት ከጨዋታ ውጤት በላይ ተመነዘረ።

በአዲሱ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ይህ ፉክክር በዓለም ስፖርት ውስጥ ካሉ ታላላቅ ግጥሚያዎች አንዱ ተደርጎ ታወቀ። ቆይቶ ደግሞ በሜዳ ዳርቻ የፔፕ ጋርዲዮላ እና የጆሴ ሞሪንሆ ፍጥጫ ሲጨመርበት፣ በሜዳ ውስጥ ደግሞ የሊዮኔል ሜሲ እና የክርስቲያኖ ሮናልዶ ፉክክር ሲታከልበት የኤል ክላሲኮ ደረጃ የበለጠ ከፍ አለ። ለእግር ኳሱም አዲስ ዘመን አበሰረ ይላል አልጀዚራ።

የሁለቱ ክለቦች ፍልሚያ በደረሰ ቁጥጥር በሜዳ እና ከሜዳ ውጭ የሚፈጠረው ጉዳይ በጉጉት ይጠበቃል። የዋና ከተማዋ የማድሪድ እና የካታሎን ፖለቲካ ይዳሰሳል። የንጉሣውያን ቤተሰብ አኗኗር እና የካታሎን ሕይወት ይነካካል።

ይህ ከጨዋታ ባሻገር የኾነ ግጥሚያ ለዓመታት እንደተወደደ ዘልቋል። እስካሁን ባደረጓቸው 263 ግጥሚያዎች ሪያል ማድሪድ 106 ጊዜ አሸንፏል። ባርሴሎና ደግሞ 105 ጊዜ ድል ቀንቶታል። 52 ጊዜ አቻ ወጥተዋል።

ዛሬ ደግሞ 264ኛው ግጥሚያቸው ይካሄዳል። የዛሬው ጨዋታም የተለየ መልክ አለው። ባርሴሎና የስፔን ላሊጋን ለማሸነፍ፤ ሪያል ማድሪድ ደግሞ በባላንጣው ተሸንፎ ባላንጣው የዋንጫ አሸናፊ ሲኾን ላለማየት የሚያደርጉት ብርቱ ፉክክር።

በውስጣዊ ችግሮች እና በሜዳ ላይ የብቃት መውረድ የተወጠረው ሪያል ማድሪድ ወደ ካታሎን አቅንቶ የምንጊዜም ባላንጣውን ይገጥማል። ዛሬ ከተሸነፈ ባርሴሎና የስፔን ላሊጋን አሸናፊ መኾን ይችላል። ይህን ማድረግ ከሽንፈትም በላይ የሚያም ሽንፈት ነው።

ቢቢሲ ኤል ክላሲኮ መቼም ቢኾን ተራ ግጥሚያ አይደለም፤ ዛሬ በባርሴሎና እና በሪያል ማድሪድ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ከወትሮው በተለየ ትልቅ ትርጉም አለው ይላል። ባርሴሎና በተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ የ11 ነጥብ ብልጫ አለው። ዛሬ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ ካሸነፈ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የላሊጋው አሸናፊ መኾኑን ያረጋግጣል ይላል ቢቢሲ። ይህን በማድሪድ ላይ ካደረገው ደግሞ የተለየ ትርጉም አለው።

ሪያል ማድሪድ ወደ ጨዋታው የሚሄደው እየጨመረ በመጣ ጫና ውስጥ ኾኖ ነው የሚለው ቢቢሲ በተጫዋቾች አለመግባባት እና በውስጣዊ የሥነ ምግባር ችግር ውስጥ ተሞልቶ ነው ይላል። የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች ኮከቡ ኪሊያን ሜባፔን ከክለባችን ይውጣ የሚለው የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻም ሌላኛው የሪያል ማድሪድ ፈተና ነው።

ሪያል ማድሪድ በቀውስ ውስጥ ኾኖ ገናናውን ጨዋታ ሲያደርግ የተረጋጋው ባርሴሎና ደግሞ በደጋፊው ፊት የዋንጫ ዘውዱን ለመድፋት ይጫወታል። ሪያል ማድሪድ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፉ ክብሩን ለመጠበቅ እና የባርሴሎናን የላሊጋ ድል ያዘገየው ይኾናል እንጂ ባርሴሎና ዋንጫውን ማሸነፉ የሚቀር አይመስልም። ሊጠናቀቁ ጥቂት በቀሩት የላሊጋ ጨዋታዎች ባርሴሎና በነጥብ ርቋልና።

ገናናው ሪያል ማድረግ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ያለ ትልቅ ዋንጫ ውድድሩን ለማጠናከር ተቃርቧል። ይህ ደግሞ ለማድሪድ ክብር እና ታሪክ የማይመጥን ነው።

ዛሬ ምሽት 4:00 ላይ የሚካሄደው ከጨዋታ በላይ የኾነው ግጥሚያ ምን ያስመለክት ይኾን? በጉጉት ይጠበቃል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

#ኤል ክላሲኮ #እግር_ኳስ #ባርሴሎና #ሪያል_ማድሪድ #ስፖርት #መዝናኛ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here