ማንቸስተር ዩናይትድ የኮቢ ሜይኖን ውል አራዘመ።

0
89
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማንቸስተር ዩናይትድ የኮቢ ሜይኖን ውል ማራዘሙን አስታውቋል።
የማንቸስተር ዩናይትድ አካዳሚ ፍሬ የኾነው ኮቢ ሜይኖ እ.አ.አ እስከ ሰኔ 2031 ድረስ የሚያቆየውን ውል ነው ያራዘመው።
ማንቸስተር ዩናይትድ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት ኮቢ ሜይኖ በእርሱ ትውልድ ካሉ ምርጥ ባለ ተሰጥኦዎች መካከል አንደኛው መኾኑን ገልጿል።
ሜይኖ ከስድስት ዓመቱ ጀምሮ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ቁርኝት ነበረው። እ.አ.አ በ2014 ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር የኾነውን የክለቡን አካዳሚ ተቀላቅሏል።
በማንቸስተር ዩናይትድ አስደናቂ ተሰጥኦውን እያሳየ የሚገኘው አማካዩ በቀጣይ ዓመታትም የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች እንደሚኾን ይጠበቃል።
ኮቢ ሜይኖ ከፊርማው በኋላ ባስተላለፈው መልዕክት ማንቸስተር ዩናይትድ ሁልጊዜም ቤቴ ነው፤ ይህ ልዩ ክለብ ለቤተሰቤ የሁሉም ነገር ትርጉም ነው፤ ይህን ማሊያ መልበስ የሚጠይቀውን ኀላፊነት በደስታ እቀበላለሁ ብሏል።
ጉዞው እስካሁን ድረስ አስገራሚ መኾኑንም ገልጿል። በስድስት ዓመቴ የመጀመሪያውን የልምምድ ክፍለ ጊዜ ስቀላቀል ከነበረኝ የማሸነፍ ፍላጎት ጋር በየቀኑ ሕልሜን የመኖር ዕድል አግኝቻለሁ ነው ያለው።
በክለቡ ውስጥ እየተገነባ ያለውን መነቃቃት ሁላችንም ይሰማናል ያለው ተጫዋቹ ማንቸስተር ዩናይትድ በሚቀጥሉት ዓመታት ለዋና ዋና ዋንጫዎች በቋሚነት እንዲታገል የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት እና ወደፊት ለመራመድ ቁርጠኛ ነኝ ብሏል።
የማንቸስተር ዩናይትድ የእግር ኳስ ዳይሬክተር ጄሰን ዊልኮክስ ኮቢ ሜይኖ በዓለም ላይ ካሉ ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ ካላቸው ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾች አንዱ ነው ብለዋል።
የእርሱ ቴክኒካዊ ብቃት፣ ቁርጠኛ ሙያዊ ብቃት እና ትሁት ስብዕናው ለወጣት ተጫዋቾቻችን ፍጹም አርዓያ፣ ለታላቁ አካዳሚያችን እውነተኛ ኩራት ያደርገዋል ነው ያሉት።
ኮቢ ቆይታውን በማራዘሙ ደስተኞች ነን፤ እሱም በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ ተጫዋቾች አንዱ ኾኖ እንደሚያድግ እና ትልልቅ ክብርን በሚያልመው የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን ውስጥ ወሳኝ ሚና ለመጫወት ዝግጁ እንደሚኾን ሙሉ ዕምነት አለን ብለዋል።
ኮቢ ሜይኖ በአሠልጣኝ ሩበን አሞሪም ዘመን የመሰለፊያ ጊዜ በማጣቱ ክለቡን ለመልቀቅ ተቃርቦ ነበር።
አሠልጣኝ ሩበን አሞሪም ተሰናብተው አሠልጣኝ ማይክል ካሪክ ክለቡን ከተረከቡ በኋላ የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች መኾኑን አሳይቷል። እያሳየው ባለው ድንቅ ብቃት እና ተሰጥኦም በክለቡ ለረጅም ጊዜ የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here