አሮን ራምሴ ራሱን ከእግር ኳስ ጨዋታ አገለለ።

0
24
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞው የአርሰናል እና የዌልስ ብሔራዊ ቡድን አማካይ አሮን ራምሴ ራሱን ከእግር ኳስ ጨዋታ አግልሏል።
የ35 ዓመቱ አሮን ራምሴ ለ20 ዓመታት የዘለቀው የተጫዋችነት ዘመኑ ማብቃቱን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በሰፈረው መልዕክት አስታውቋል።
በካርዲፍ ሲቲ የታዳጊዎች ቡድን ውስጥ መጫወት የጀመረው አሮን ራምሴ የሰሜን ለንደኑን ክለብ አርሰናልን ለ11 ዓመታት በተጫዋችነት አገልግሏል። ጁቬንቱስ፣ ኒስ፣ ሬንጀርስ እና በቅርቡ ደግሞ ለሜክሲኮው ፑማስ ተጫውቷል።
በአርሰናል ቤት 369 ጨዋታዎችን አድርጓል። 64 ግቦችን አስቆጥሯል። ሦሥት የኤፍ ኤ ዋንጫዎችን አሳክቷል። በተለይ እ.አ.አ በ 2014 እና 2017 የኤፍ ኤ ዋንጫዎች የማሸነፊያ ግቦችን በማስቆጠር ይታወሳል። የኮሚዩኒቲ ሽልድ ዋንጫንም ማሳካት ችሏል። በጁቬንትስ ደግሞ የሴሪኤ ዋንጫን አሸንፏል።
ራምሴ ለሀገሩ ዌልስ ብሔራዊ ቡድን 86 ጨዋታዎችን አድርጎ 21 ግቦችን አስቆጥሯል። በዩሮ 2016 ዌልስ ለግማሽ ፍጻሜ እንድትበቃም ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
አሮን ራምሴ በአርሰናል ደጋፊዎች ተወዳጅ ተጫዋች ነበር።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከሜክሲኮው ክለብ ፑማስ ጋር ተለይቶ ክለብ አልባ ኾኖ የቆዬው ራምሴ ከጉዳት ጋር ሲታገል ቆይቷል። ጉዳት ከተጫዋችነት ራሱን እንዲያገል እንዳደረገው ገልጿል።
ራምሴ የተጫዋችነት ዘመኑ መጠናቀቁን ባስታወቀበት መልዕክቱ ውሳኔው ቀላል እንዳልነበር ገልጿል። ለቤተሰቦቹ፣ ለተጫወተባቸው ክለቦች እና ለደጋፊዎቹ ምሥጋና አቅርቧል። ራምሴ በቀጣይ ወደ አሠልጣኝነት ሥራ ሊያመራ እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥቷል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here