ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሀሪ ማጓየር በማንቸስተር ዩናይትድ እስከ 2027 የሚያቆየውን ውል አራዝሟል።
በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ላይ ውሉ የሚጠናቀቀው ሀሪ ማጓየር ለተጨማሪ አንድ ዓመት ነው ውሉን ያራዘመው። በውሉ ላይ ተጨማሪ አንድ ዓመት የማራዘም ስምምነት እንዳለም ቢቢሲ ዘግቧል።
ሀሪ ማጉየር እ.አ.አ በ2019 ነበር ከሌስስተር ሲቲ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ያቀናው። በወቅቱ የተከፈለበት 80 ሚሊዮን ፓውንድ ለተከላካይ ተጫዋቾች የተከፈለ ክብረ ወሰን ነው።
በማንቸስተር ዩናይትድም አምበል ኾኖ ተጫውቷል። ነገር ግን ተጫዋቹ በመካከል ባሳየው የአቋም መውረድ አምበልነቱን ተነጥቋል። ክለቡንም ይለቃል ተብሎ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እያሳየው ባለው ብቃት ክለቡ የውል ማራዘሚያ አቅርቦለታል።
ሀሪ ማጓየርም የቀረበለትን የአንድ ዓመት ውል ፈርሟል። በክለቡም እሰከ 2027 ይቆያል። በውሉ ላይ እስከ 2028 ማቆየት የሚያስችል አንድ ዓመት የማራዘም ስምምነት እንዳለም ተገልጿል።
ሀሪ ማጓየር ከፊርማው በኋላ ባስተላለፈው መልዕክትማንቸስተር ዩናይትድን ወክሎ መጫወት ክብር ነው፤ እኔ እና ቤተሰቤ በየቀኑ የምንኮራበት ኀላፊነት ነው ብሏል። በዚህ አስደናቂ ክለብ ውስጥ ያለኝን ጉዞ በማራዘሜ ደስተኛ ነኝ ነው ያለው።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



