ባሕርዳር፡ መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ይጀምራሉ።
በተከታታይ ከሀገር ውስጥ ሁለት ዋንጫዎች የተሰናበተው አርሰናል ወደ ፖርቹጋል አቅንቶ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር ይጫወታል።
ቢቢሲ በዘገባው የዛሬው ጨዋታ አርሰናል በካራባኦ ካፕ እና በኤፍ ኤ ዋንጫ የገጠሙትን ሽንፈቶች የሚረሳበት ጨዋታ እንደሚኾን ይጠበቃል ብሏል። ነገር ግን በስፖርቲን ሊዝበን ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል።
በዛሬው ጨዋታ ጁሪየን ቲምበር እና ቡካዮ ሳካ እንደማይኖሩ ፋብሪዚዮ ሮማኖ በዘገባው አመላክቷል። የሁለቱ ወሳኝ ተጫዋቾች በጨዋታው አለመኖር ለአርሰናል ሌላ ፈተና ነው። ጨዋታው ምሽት 4:00 ይካሄዳል።
የምሽቱ ታላቁ ጨዋታ በስፔን ማድሪድ ይካሄዳል። የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ንጉሡ ሪያል ማድሪድ የጀርመኑን ኀያል ክለብ ባየርን ሙኒክን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ይጋብዛል።
ይህ ጨዋታ የዓለም እግር ኳስ ወዳጆችን ትኩረት ስቧል። የከዋክብቶች ፍጥጫ የሚደረግበት ይህ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል። ቢ ሶኮር በዘገባው የኀያላኑ ግጥሚያ ትኩረት እንደሚስብ አመላክቷል።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ንጉሡ ማድሪድ ባለፉት ዓመታት በባየርን ሙኒክ ላይ የበላይነት አለው። ዛሬም በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የሚያደርገውን ጨዋታ በበላይነት እንደሚወጣ ይጠበቃል። ነገር ግን በዘንድሮው የውድድር ዘመን የሪያል ማድሪድ እና የባየርን ሙኒክ አቋም በተለያየ ከፍታ ላይ ነው። ማድሪድ የቀድሞው ግርማው የራቀው ሲመስል ባየርን ሙኒክ በአስደናቂ አቋም ላይ ይገኛል።
ይህ ኾኖ ወደቀ ሲባል የሚነሳው ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ያለውን ልምድ እና ታሪክ እንደሚጠቀም ይጠበቃል።
ቢ ሶከር በዘገባው ሪያል ማድሪድ ከባየርን ሙኒክ ጋር ባደረጋቸው ያለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች አልተሸነፈም ብሏል። በሰባት ጨዋታዎች ድል ሲያደርግ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ዛሬም የሻምፒዮንስ ሊግ ግርማ ሞገሱን ይጠቀማል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያለው።
አጓጊው ጨዋታ ምሽት 4:00 ይካሄዳል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



