ይህ ከእግር ኳስ የተሻገረ ድል ነው።

0
5
ባሕር ዳር: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ይህች ተፈጥሮ ያደላት፤ በሃብት የመላት ሀገር በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች፤ አያሌ የመከራ ዘመናትን ተሻግራለች፤ ተፈጥሮ የሰጣት ጸጋ ቅኝ ገዥዎችን እና አምባገነን መሪዎችን እያስነሳ በጭንቅ ውስጥ እንድትኖር ሲያደርጋት ኖሯል።
ሀብቶቿን የሚፈልጉ ሁሉ በኃይል እየተነሱ ሲያደሟት ኖረዋል። ለረጅም ዓመታት የዘለቀ የእርሰ በእርስ ግጭት አድምቷታል፤ በአማፂ ቡድኖች እና በመንግሥት ኃይሎች የሚካሄዱ ውጊያዎች አቁስለዋታል።
ቀጣናዊ ግጭቶች፣ ስልታዊ ሙስና፤ የሀገሪቱን ሃብት በአግባቡ አለመጠቀም፤ በተደጋጋሚ የተነሱ ወረርሽኞች እንደጅራፍ የገረፏት ፈተናዎች ናቸው። የቀድሞዋ ዛየር የአሁኗ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ።
አልማዝ፣ ወርቅ እና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ያሉባት ሀገር እንደኾነች ይነገራል። ነገር ግን እነዚህን ሃብቶቿን ተረጋግታ መጠቀም ያልቻለት ሀገር ናት።
ይህች ፈተና የማያጣት ሀገር የሚያደሟት ግጭቶችን፤ የሚፈትኗት ወረርሽኞችን፤ በሃብቷ ምክንያት የሚነሱባት ጠላቶችን እየታገለች የእግር ኳስ ስፖርትን እያሳደገች ነው።
ከቅርብ ዓመታት በኋላ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድንን እያስመለከተች ያለችው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትናንት አመሻሽ በአሕጉራት የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ ጃማይካን በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫ አልፋለች።
ይህ ድሏ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ቆይቶ የተገኘ ነው። የአሁኗ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀድሞዋ ዛየር በታሪክ በዓለም ዋንጫ የተሳተፈችው ከ52 ዓመታት በፊት እ.አ.አ በ1974 ነበር።
በእርግጥ በዚያ ዘመን ታሪክ ሠርታ በዓለም ዋንጫው ብትሳተፍም በምድብ ጨዋታዎች ያሳየችው አቋም ደካማ ነበር። እስከ ዓለም ዋንጫው የደረሰችበት የተጋድሎ ታሪክ ግን አይረሳም።
ቢቢሲ ኮንጎ ትናንት ያሳካችውን ድል ይህ ከእግር ኳስ በላይ ነው ይላል። የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደጋፊዎች ለ52 ዓመታት ይሄን ድል ሲናፍቁ ኖረዋል ሲልም ገልጿል።
ኮንጎን ወደ ዓለም ዋንጫ የወሰደቻትን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው አክስል ቱዋንዛቤ ከጨዋታው በፊት በሰጠው አስተያየት ይሄን ጨዋታ በእርግጠኝነት በእግር ኳስ ሕይወቴ ውስጥ ትልቁ ጨዋታ አድርጌ እቆጥረዋለሁ ብሎ ነበር። እንዳለውም በሕይወቱ ትልቁን ጨዋታ አድርጎ የ52 ዓመታት ታሪክ የቀየረች ግብ አስቆጥሮ አዲስ ታሪክ ጽፏል።
ኮንጎ በታሪኳ ውስጥ በትልቁ የሚነገር ድል አስመዝግባ ወደ ዓለም ዋንጫው ስትሻገር እነዚያ ፈተና የገፋቸው ዜጎቿ በደስታ ቦርቀዋል።
የዚያኔዋ ዛየር የአሁኗ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እ.አ.አ በ1974 የዓለም ዋንጫ ስትደርስ ከሰሃራ በታች የመጀመሪያዋ ሀገር በመኾን ነበር።
ይህች ግዙፍ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች ከእርሷ በብዙ የሚያንሱ ሀገራት ወደ ዓለም ዋንጫው በተደጋጋሚ ሲያልፉ እርሷ ግን የቀደመ ታሪኳን እያሰበች በቅናት ኖራለች።
በሙስና እና ብለሹ አሠራር፤ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና ሌሎች ግጭቶች የኮንጎን እግር ኳስ ጎድቶት ኖሯል። ከቅኝ ግዛት እስር ወጥታ ወደ ሌላ የማያባራ ግጭት ውስጥ የተሻጋገረችው ኮንጎ እግር ኳሷ እንዲዳከም፤ የእግር ኳስ መሠረተ ልማቶች እንዳይሠሩ አድርጎ ቆይቷል ይላል ቢቢሲ።
አሁን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኋላ የተገኘው ድል ለኮንጎ ዝም ብሎ የእግር ኳስ ድል አይደለም። ይልቅስ ተስፋ፣ የአንድነት ምንጭ፣ ጽናት እና ይቻላልን የሚያሳይ፤ ለኮንጓውያን ከዓመታት በኋላ የተሰጠ የደስታ ስጦታ ነው እንጂ።
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጨዋቾች እግር ኳስ ለሀገሪቱ የሰላም አየርን የሚሰጥ ነው ይሉታል።
በውጭ ሀገራት የተወለዱ እና በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚጫወቱ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጨዋቾች ለሀገሪቱ እግር ኳስ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል ይላል ቢቢሲ።
እነዚህ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት የተወለዱት ነገር ግን የዘር ሀረጋቸውን ቆጥረው ለብሔራዊ ቡድናቸው የተሰለፉ ተጨዋቾች በአንድነት ኮንጎን ከፍ አድርገዋል። ፈተና ለበዛባት ሀገር አዲስ ባለተስፋም ኾነዋል።
ኒውዮርክ ታይምስ በፈተና ውስጥ ለሚገኙት ኮንጓውያን የተሰጠ ድል እንደኾነ ጽፏል። ደጋፊዎች የትናንቱን ጨዋታ በአንድነት እየዘመሩ ተመለከቱት፤ እየሳቁም ወደቤታቸው ተመለሱ። ይህ ደስታ የአንድ ቀን ብቻ አይደለም፤ በኮንጓውያን ልብ ውስጥ ቀጣይነት አለው እንጂ።
ኒውዮርክ ታይምስ በዘገባው ይህ ድል ባለፉት ዓመታት በችግር ውስጥ ላለፉት ኮንጓውያን ይገባቸዋል፤ ለተሰቃዩት፣ አሁንም ለሚሰቃዩት ሽልማት ነው ይላል።
አሁን ማድረግ የሚገባቸውን ሁሉ አድርገዋል፤ በዓለም ፊት በሰላም መድረክ በአንድነት ቆመዋል፤ አንድነታቸው በሰጣቸው ፍሬ እየተደሰቱ ነው። አንዳንድ ጨዋታዎች ከእግር ኳስ በላይ ናቸው። ብዙ ጉዳዮችን ይቀይራሉ፤ ተስፋ እና አንድነትን ያመጣሉና።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here