አዲስ አበባ: መጋቢት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለ23ኛው የዓለም ዋንጫ የሚሳተፉ ቀሪ ስድስት ብሔራዊ ቡድኖች ትናንት ምሽት መታወቃቸውን ተከትሎ በዚህ ክረምት በሚካሄደው ውድድር ላይ የሚሳተፉ የ48ቱ ሀገራት ዝርዝር ተሟልቷል።
በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ ከሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኢራቅ የመጨረሻዎቹን ሁለት ቦታዎች የያዙ ሀገራት ኾነዋል።
ይህም ከመስከረም 2016 ጀምሮ በስድስት ኮንፌዴሬሽኖች ስር ሲካሄድ የቆየውን እና መጋቢት 22 በአውሮፓ እና በአህጉራት አቀፍ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የተጠናቀቀውን ረጅም የማጣሪያ ጉዞ አሳርጓል።
በመጨረሻው ቀን አራት የአውሮፓ ብሔራዊ ቡድኖች ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። የዕለቱ ትልቁ ዜና የነበረው የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጣሊያን በቦስኒያ ሄርዞጎቪኒያ ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ መኾኗ ነው። ከቦስኒያ በተጨማሪ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ቱርክ እና ስዊድን ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጃማይካን፣ ኢራቅ ደግሞ ቦሊቪያን በማሸነፍ ነው ለውድድሩ የበቁት።
በውድድሩ ላይ ከሚካፈሉት 48 ቡድኖች መካከል ሦሥቱ አስተናጋጅ ሀገራት በቀጥታ አልፈዋል። 43ቱ በየኮንፌዴሬሽናቸው በነበረው የማጣሪያ ጨዋታ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ በአህጉራት አቀፍ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የተወሰኑ ናቸው።
አሁን የተሳታፊዎች ዝርዝር ሙሉ በሙሉ በመታወቁ ትኩረት ሁሉ እስካሁን ከታዩት የዓለም ዋንጫዎች በትልቅነቱ ወደሚለየው የዘንድሮው ውድድር አቅንቷል።
ውድድሩ እንዴት ይካሄዳል? ከአራት ዓመት በፊት በኳታር በነበሩት 32 ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ጭማሪ ተደርጎ የ2026ቱ ውድድር በታሪክ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ 48 ሀገራት የሚሳተፉበት ኾኗል፤ ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ሀገራት ውስጥ የሚደረጉ 104 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።
ውድድሩ ከሰኔ 4 እስከ ሐምሌ 12 ባለው ጊዜ ውስጥ በ16 ከተሞች ይካሄዳሉ። በአሜሪካ በ11 ከተሞች፣ በሜክሲኮ በ3 ከተሞች እና በካናዳ በ2 ከተሞች ነው ጨዋታዎች የሚካሄዱት።
ውድድሩ ለ39 ቀናት ይቆያል። ይህም በኳታር ከነበረው 29 ቀናት፣ በ2014 እና 2018 ከነበረው 32 ቀናት የረዘመ ያደርገዋል፣ አዲሱ አወቃቀር ደግሞ እያንዳንዳቸው አራት ቡድኖችን የያዙ 12 ምድቦችን ያካትታል።
ውድድሩ በዕለተ ሐሙስ ሰኔ 4 ጅማሮውን ሲያደረግ ሜክሲኮ በሜክሲኮ ሲቲው ኢስታዲዮ አዝቴካ ደቡብ አፍሪካን በመግጠም ውድድሩን ትከፍታለች።
ከ12ቱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ ቡድኖች በደረጃቸው የተሻሉ ስምንት ሦሥተኛ የወጡ ሀገራት ከ32 ቡድኖች ጀምሮ ወደሚካሄደው ሰፊ የማጣሪያ ምዕራፍ ያልፋሉ።
በአዲስ መልኩ በርካታ ብሔራዊ ቡድኖችን የሚያሳትፈው የዓለም ዋንጫ ሐምሌ 12 በአሜሪካ ኒው ጀርሲ ሜትላይፍ ስታዲየም ፍጻሜውን ያገኛል ሲል ያስነበበው ቢቢሲ ነው።
ዘጋቢ፦ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



