ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ የቶተንሃም ሆትስፐርስ አሠልጣኝ ኾነው ተሹመዋል።
ከቀናት በፊት ጊዜያዊ አሠልጣኙን ኢጎር ቱዶርን ያሰናበተው ቶተንሃም ሮቤርቶ ዲ ዘርቢን ሾሟል። ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ በዓመቱ ቶተንሃምን የሚያሰለጥኑ ሦስተኛው አሠልጣኝ ይኾናሉ።
አሠልጣኙ የመውረድ ስጋት ያለበትን ቶተንሃምን የማትረፍ ኀላፊነት ተሰጥቷቸዋል። ቢቢሲ በዘገባው ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ የቶተንሃም አሠልጣኝ ለመኾን የረጅም ጊዜ ውል ተፈራርመዋል ብሏል። አሠልጣኙ በቶተንሃም ቤት ለአምስት ዓመታት እንደሚቆዩም ይጠበቃል።
ሰባት ጨዋታዎች ብቻ በቀሩት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከወራጅ ቀጣናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቆ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አዲሱ አሠልጣኝ በቀሪ ጨዋታዎች ቶተንሃምን ወደ አሸናፊነት በመመለስ ከመውረድ እንደሚታደጉት ይጠበቃል።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ድል ካደረገ ወራቶች ተቆጥረዋል።
ቶተንሃም ሆትስፐርስ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት ሮቤርቶ ዲ ዘርቢን በረጅም ጊዜ ውል አዲሱ ዋና አሠልጣኝ አድርገን መሾማችንን በደስታ እናሳውቃለን ብሏል።
አዲሱ አሠልጣኝም በዓለም ላይ ታዋቂ ከኾኑ ክለቦች መካከል አንዱን በመቀላቀሌ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
ታላላቅ ስኬቶችን ማሳከት የሚችል ክለብ ለመገንባት ደጋፊዎችን ለማስደሰት መምጣታቸውንም ገልጸዋል።
በአጭር ጊዜ ቅድሚያ የሚሰጡት ቶተንሃምን ካለበት የደረጃ ሠንጠረዥ ማውጣት እንደኾነም አንስተዋል። ከተጫዋቾች ጋር በልምምድ ሜዳ እስከሚገናኙ መቸኮላቸውንም ተናግረዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



