ባሕር ዳር: መጋቢት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በየአራት ዓመቱ የሚደረገው ታላቁ የዓለም ሀገራት እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር እስካሁን ለ22 ጊዜያት ተካሂዷል፡፡ 23ኛው መድረክ ደግሞ ከሦሥት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በጥምረት ይስተናገዳል፡፡
የዓለም ዋንጫን ታላቅነት ማሳያ ከኾኑት ጉዳዮች ውስጥ የበርካታ ተመልካቾች ቁጥር አንዱ ኾኖ ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ረገድ በእስከዛሬ ውድድሮች የተመዘገቡ አሀዛዊ ክብረ ወሰኖችን እንመልከት፡፡
እስካሁን በተካሄዱት 22 የዓለም ዋንጫዎች በስታዲየም በታደሙ ተመልካቾች ቁጥር ክብረወሰኑን የያዘው እ.አ.አ በ1994 ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደችው ውድድር ነው፡፡ በዚያ ውድድር በተካሄዱት 52 ጨዋታዎች በድምሩ 3 ሚሊዮን 585 ሺህ 538 ተመልካቾች ታድመዋል፡፡
ይህ ቁጥር በአንድ ጨዋታ በአማካኝ 68 ሺህ 991 ተመልካቾች እንደተገኙ የሚያመላክት ነው። ብራዚል ጣሊያንን በፍጹም ቅጣት ምት አሸንፋ የውድድሩ አሸናፊ በኾነችበት የፍጻሜው ጨዋታ ብቻ 94 ሺህ 194 ተመልካቾች በሎስ አንጀለሱ ሮዝ ቦውል ስታዲየም ታድመዋል፡፡
ባለፉት አራት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች በያንዳንዳቸው ከ3 ሚሊዮን በላይ አጠቃላይ የተመልካች ቁጥር ቢመዘገብም የ1994ቱን ክብረወሰን የሰበረ ግን እስካሁን አልተገኘም፡፡ ምናልባት የተጠጋው ቢኖር ብራዚል ባስተናገደችው የ2014ቱ መድረክ የተመዘገበው 3 ሚሊዮን 441 ሺህ 450 የተመልካች ቁጥር ነው፡፡
በአንድ ጨዋታ ብቻ በተመዘገበ ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር ደግሞ የ1950ው የፍጻሜ ጨዋታ ክብረወሰኑን ይዞ እናገኘዋለን፡፡ ብራዚል ባስተናገደችው እና ኡራጓይ አስተናጋጇን ሀገር ባልተጠበቀ ውጤት 2ለ1 አሸንፋ የዋንጫ ባለቤት በኾነችበት በዚያ የፍጻሜ ጨዋታ 173 ሺህ 850 ተመልካቾች በታላቁ የማራካኛ ስታዲየም ተገኝተው ተከታትለዋል፡፡
ከዚያ ውጭ በአንድ ጨዋታ ከ100 ሺህ በላይ ተመልካቾች በስታዲየም የታደሙባቸው ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከነዚህም አንዱ በ1986 ሜክሲኮ ላይ በተካሄደው ውድድር አርጀንቲና የቀድሞዋን ምዕራብ ጀርመንን አሸንፋ ዋንጫውን ባነሳችበት የፍጻሜ ጨዋታ 114 ሺህ 600 የተመልካች ቁጥር ተመዝግቧል፡፡
እዚያው ሜክሲኮ ላይ በተስተናገደው የ1970 ውድድር ደግሞ አስተናጋጇ ሜክሲኮ ቤልጅየምን 1ለ0 የረታችበትን ጨዋታ 108 ሺህ 192 ተመልካቾች በስታዲየም ተከታትለውታል፡፡ ያሆ ስፖርት እንደዘገበው አስገራሚው ነገር ይሄኛው ጨዋታ እንደሌሎቹ የፍጻሜ ሳይኾን በምድብ ማጣሪያ የተደረገ መኾኑ ነው፡፡
ዘጋቢ፦ኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



