ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አሁን ላይ የሀገራት እግር ኳስ ጨዋታዎች እየተደረጉ ነው። ለሀገራቸው ብሔራዊ ቡድን ጥሪ የደረሳቸው ተጫዋቾች ወደ ሀገራቸው ተጉዘዋል። የሀገራቸውን መለያ ለብሰውም እየተጫወቱ ነው።
ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች በርካታ ተጫዋቾችን ያሰመረጠው አርሰናል ተጫዋቾቹ እየተጎዱበት ነው። እስካሁን ድረስ 11 ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት የሀገራቸውን ብሔራዊ ቡድን ለቅቀው ወደ ለንደን እየተመለሱ ነው።
በጉዳት ምክንያት ከየብሔራዊ ቡድናቸው የወጡት የአርሰናል ተጫዋቾች ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የሚርቁ ከኾነ አርሰናል ጫና ውስጥ ይገባል። ለሦስት ዋንጫዎች እየተፎካከረ የሚገኘው አርሰናል ያለ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ለዋንጫ ለመፎካከር ይቸገራል።
ዴይሊ ሜል በዘገባው 11 የአርሰናል ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድን ወጥተዋል ብሏል።
አምበሉ ማሪቲን ኦዲጋርድ ከኖሩዌይ ብሔራዊ ቡድን፣ ሌአንድሮ ትሮሳርድ ከቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን፣ ዊሊያም ሳሊባ ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን፣ ጋብርኤል ማጋሌሽ ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን፣ ጁሪዬን ቲምበር ከኔዘርላንድ ብሔራዊ ቡድን፣ ኤብሪች ኤዜ፣ ዲክላን ራይስ፣ ቡካዮ ሳካ እና ኖኒ ማዱኤኬ ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን፣ ፒይሮ ሂንካፔ ከኢኳዶር ብሔራዊ ቡድን እና ማርቲን ዙቢሜንዲ ከስፔን ብሔራዊ ቡድን የወጡ ተጫዋቾች ናቸው።
አርሰናል በፊፋ ቫይረስ እየተጠቃ ነው። ይህ ደግሞ ለአሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ራስ ምታት ነው። ፉትቦል ለንደን በዘገባው የአርሰናል የዋንጫ ውድድር አደጋ እየገጠመው ነው ብሏል። በርካታ ተጫዋቾች በጉዳት ምክንያት ከብሔራዊ ቡድን መራቅ ለእርሳቸው አደጋ መኾኑን ገልጿል።
አንዳንዶች ግን የአርሰናል ተጫዋቾች ከብሔራዊ ቡድን የወጡት ለጥንቃቄ እንጂ በጉዳት ምክንያት አይደለም እያሉ ነው። አብዛኛዎቹ ጨዋታዎች የወዳጅነት በመኾናቸው ተጫዋቾቹ ለጉዳት እንዳይዳረጉ ከአደጋ የማራቅ ስልት ነው እየተባለም ይገኛል።
የአርሰናል ተጫዋቾች የእውነት ጉዳት ወይስ? ለጥንቃቄ የተደረገ ሽሽት?
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



