ባሕር ዳር : መጋቢት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እስካሁን በተካሄዱት 22 የዓለም ሀገራት እግር ኳስ ዋንጫ ውድድሮች አምስት ጊዜ አሸናፊ የኾነችውን ብራዚልን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ዋንጫውን አሸንፈዋል።
በ1930 በተካሄደው የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ኡራጓይን ይዘው ባለድል ከኾኑት አልቤርቶ ሱፒቺ እስከ የ2022ቱ ውድድር ከአርጀንቲና ጋር ባለድል ከኾኑት ሊዮኔል ስካሎኒ ድረስ 21 አሠልጣኞች የዓለም ዋንጫ ድልን አጣጥመዋል፡፡
አንድ አሠልጣኝ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ለመኾን ከሚያስፈልጉት ብቃቶች ውስጥ የሥብሥብ ጥራት፣ የማቀናጀት ጥበብ፣ የታክቲክ ክህሎት፣ የአሸናፊነት ሥነልቦና እና በተወሰነ ደረጃ ዕድል ይጠቀሳሉ፡፡
ኾኖም ከእነዚህ ሁሉ በላይ የሀገር ውስጥ አሠልጣኝነት የላቀ ሚና እንዳለው ያለፉት የዓለም ዋንጫ ውድድሮች አሳይተዋል፤ 21ዱም አሠልጣኞች የዓለም ዋንጫን ያነሱት የሀገራቸውን ብሔራዊ ቡድን ይዘው ነውና።
ከእነዚህ አሠልጣኞች ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ አሸናፊ በመኾን ታሪክ የሠሩት ግን አንድ ሰው ብቻ ናቸው፡፡ጣሊያናዊው አሠልጣኝ ቪቶሪዮ ፓዛ በ1934 እና 1938 የሀገራቸውን ብሔራዊ ቡድን በተከታታይ አሸናፊ በማድረግ ታሪክ ሠርተዋል፡፡
ከጣሊያናዊው አሠልጣኝ ቪቶሪዮ ፓዛ ውጭ አንድ ጊዜ ሀገራቸውን ባለድል ያደረጉ አምስት አሠልጣኞች በሌላ የዓለም ዋንጫ ሁለተኛ ደረጃን እየያዙ አጠናቅቀዋል፡፡ከሀገራቸው ውጭ ሌሎች በርከት ያሉ ሀገራትን ይዘው በዓለም ዋንጫ በመሳተፍ ረገድ ደግሞ ብራዚላዊውን አሠልጣኝ ካርሎስ አልቤርቶ ፔሬራን የሚስተካከላቸው የለም፡፡
በ1994 አሜሪካ ላይ በተካሄደው ውድድር ብራዚልን አሸናፊ ያደረጉት ፔሬራ በ1982 ኩዌትን፣ በ1990 የተባበሩት አረብ ኢምሬትስን፣ በ1998 ሳዑዲ አረቢያን፣ በ2010 ደቡብ አፍሪካን ይዘው በዓለም ዋንጫው ቢቀርቡም ውጤታማ አልኾኑም፡፡በ2006ቱ መድረክ እንደገና ወደ ብራዚል ብሔራዊ ቡድን ቢመለሱም ከሩብ ፍጻሜ ያለፈ ጉዞ አልነበራቸውም፡፡
ከሀገራቸው ጋር በተጫዋችነትም በአሠልጣኝነትም አሸናፊ የኾኑ ደግሞ ሦሥት ሰዎችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው ብራዚላዊው ማርዮ ዛጋሎ በ1958 እና በ1962 በተጫዋችነት፣ በ1970 በአሠልጣኝነት የዓለም ዋንጫን አንስተዋል፡፡
ጀርመናዊው ፍራንዝ ቤከንባወር በበኩሉ በ1974 ሀገሩን በተጫዋችነት፣ በ1990 ደግሞ በአሠልጣኝነት መርቶ ባለድል አድርጓል፡፡
እንደ ያሆ ስፖርት ዘገባ በ1998 ፈረንሳይን በአምበልነት እየመራ ሻምፒዮን የኾነው ዲዲዬ ዴሾም እንዲሁ 2018 ላይ በአሠልጣኝነት ድሉን ደግሞታል፡፡
አሁን ከ77 ቀናት በኋላ በሚጀመረው የ2026 የዓለም ዋንጫስ ሀገር በቀል አሠልጣኞች ይሳካላቸው ይኾን? በነገራችን ላይ እስካሁን ማጣሪያውን ካለፉት የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሀገራት መካከል የራሳቸውን ሀገር ብሔራዊ ቡድን የያዙት አሠልጣኞች 19 ብቻ ናቸው፡፡
በኃይሌ አበራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



