78 ቀናት የቀሩት የዓለም ዋንጫ ትውስታ እና ዕድሜ ቁጥር ብቻ እንደኾነ ያስመሠከረው ተጫዋች።

0
37

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እግር ኳስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እና የአካል ብቃት የሚጠይቅ ጨዋታ በመኾኑ የአንድ ተጫዋች ብቃት እስከመጨረሻው አብሮት እንዳይዘልቅ ብዙ ጊዜ የዕድሜ ጉዳይ ተፅዕኖ ያሳድራል።

በርግጥ ይህ ለግብ ጠባቂዎች ላይሠራ ይችላል። በ30ዎቹ መጨረሻ አለፍ ሲልም እስከ 40ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ብቃታቸው ሳይወርድ የሚዘልቁ ግብ ጠባቂዎች ጥቂት አይደሉም።

በሌሎች ተጨዋቾች ግን ይሄ ብዙም የተለመደ አይደለም። በዓለም ዋንጫው ታሪክ ዕድሜ ቁጥር ብቻ መኾኑን ያስመሰከረ አንድ ተጫዋች ግን እናገኛለን። ይህም ካሜሩናዊው አጥቂ ሮጀር ሚላ ነው።

ካሜሩናዊው አጥቂ ሮጀር ሚላ በ1982ቱ የዓለም ዋንጫ ሀገሩ ማጣሪያውን አልፋ እንድትሳተፍ ከፍተኛ ሚና ከተጫወተ በኋላ ለስድስት ዓመታት ያክል ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች አግልሎ ነበር።

ኾኖም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ባሳደሩበት ግፊት ከብዙ ማሰብ እና ማንገራገር በኋላ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ተመለሰ።

እናም በ1990ው የዓለም ዋንጫ የማይበገሩት አናብስት በምድብ ጨዋታዎች ቀደም ሲል አሸናፊ የነበረችውን አርጀንቲናን ጭምር አሸንፈው በሩብ ፍጻሜ በእንግሊዝ በመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ተሸንፈው እስከተሰናበቱበት ድረስ ሮጀር ሚላ ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ አራት ግቦችን አስቆጥሯል።

በዚህም በዓለም ዋንጫው ታሪክ በ38 ዓመት ዕድሜው ግብ ያስቆጠረ በዕድሜ አንጋፋው ተጫዋች ኾኗል።

ይሄው ብቃቱም የወቅቱ የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋችነት ክብርን አጎናፅፎታል።

ከአራት ዓመት በኋላ አሜሪካ ላይ በተካሄደው የ1994ቱ መድረክም ሮጀር ሚላ እና ካሜሩን ተሳታፊ ነበሩ።

በርግጥ በዚህ ውድድር ካሜሩን ከአራት ዓመት በፊት እስከ ሩብ ፍጻሜ የተጓዘችበትን ገድል አልደገመችውም፤ ሮጀር ሚላ ግን የራሱን ታሪክ እና ክብረወሰኑን አሻሽሏል።

ከሩሲያ ጋር በተደረገው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታም በ42 ዓመት ከ39 ቀናት ዕድሜው ግብ አስቆጥሮ ክብረወሰኑን ከማሻሻል ባለፈ አሁን ድረስ ያልተነካ የዓለም ዋንጫው በዕድሜ ትልቁ ግብ አስቆጣሪነት ክብርን ጨብጧል።

ዘጋቢ፦ ኃይሌ አበራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here