ባሕር ዳር: መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዚነዲን ዚዳን ከ2026 የዓለም ዋንጫ በኋላ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኾኖ እንደሚሾም ተገልጿል።
ፈረንሳዊው የቀድሞ የእግር ኳስ ኮኮብ እና ውጤታማው አሠልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ከ2026 የዓለም ዋንጫ በኋላ የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን ለመረከብ በቃል ደረጃ መስማማቱ ተዘግቧል።
ዚዳን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን የሚረከበው ዲዲየር ዴሻምፕስን በመተካት ነው። የወቅቱ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕስ ፈረንሳይ የ2018 የዓለም ዋንጫን እንድታሸንፍ ያደረጉ ውጤታማ አሠልጣኝ ናቸው።
ዚዳን በተጫዋችነት እና በአሠልጣኝነት ውጤታማ ነው። ከሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫን ያሳከው ዚዳን በእግር ኳስ አያሌ ክብሮችን አሳክቷል። ራሱን ከተጫዋችነት ካገለለ በኋላ ሪያል ማድሪድን አሠልጥኗል።
በሪያል ማድሪድ አሠልጣኝነት ዘመኑም ማድሪድ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን እንዲያሸንፍ ያደረገ ስኬትማ አሠልጣኝ ነው። ከማድሪድ ከለቀቀ በኋላ ስሙ ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እና ከተለያዩ ክለቦች ጋር ሲያያዝ ቆይቶ ነበር።
በመጨረሻም ዚዳን የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን ለመረከብ በንግግር ደረጃ መስማማቱን ኢኤስፒኤን ዘግቧል።
ቢን ስፖርት በዘገባው ዚዳን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ለመኾን ተቃርቧል ብሏል። ፈረንሳይ የቀድሞ ኮኮቧን ለመሾም ስትሠራ መቆየቷን ያስታወሰው ዘገባው ከዓለም ዋንጫው መጠናቀቅ በኋላ ዚዳን የሀገሩን ብሔራዊ ቡድን የመርከቡ ነገር እየቀረበ መጥቷል ነው ያለው።
የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የወቅቱ አሠልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕስ ከዓለም ዋንጫ በኋላ እንደሚለቁ በማረጋገጡ ከእርሳቸው በኋላ ቡድኑን የሚረከበውን አሠልጣኝ ለማግኘት በውስጥ ሢሠራ ቆይቷል።
ቢን ስፖርት ዚዳን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ መኾኑ ከተረጋገጠ ምርጡን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የማስቀጠል ኀላፊነት ይወስዳል። ስኬታማ የኾነውን ፕሮጀክትም እንዲያስቀጥል ይጠበቃል ብሏል።
ፋብሪዚዮ ሮማኖም ዚነዲን ዚዳን የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን ለማሠልጠን ፈቃደኛ መኾኑን ገልጿል ብሏል። በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን እና በክለቦች፣ በአሠልጣኝነት በሪያል ማድሪድ አያሌ ስኬቶችን የደራረበው ዚዳን በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝነት ዘመኑስ ምን ያሳይ ይኾን?
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



