አርሰናልን ከማንቸስተር ሲቲ የሚያገናኘው የካራባኦ ዋንጫ ፍጥጫ!

0
121

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 12/2018 ዓ.ም(አሚኮ) ነገ እሑድ አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ በካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ ይገናኛሉ።

አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ በተጨዋችነት እና በአሠልጣኝነት ወቅት በዌምብሌይ ያካሄዳቸውን 12 ጨዋታዎች ሁሉንም አሸንፏል።

ፔፕ ጋርዲዮላ በአሠልጣኝነት ወደ እንግሊዝ የመጡ ጊዜ የመጀመሪያ ዋንጫቸውን ያነሱት የካራባኦ ዋንጫ ነበር። ይህም እ.አ.አ 2018 በዌምብሌይ አርሰናልስን 3ለ0 በማሸነፍ ነበር።

ይህ ክስተት የአሠልጣኝ አርሰን ቬንገር ማብቂያ እንዲሁም የሲቲ ገናናነት የጀመረበት ነበር።

ማንቸስተር ሲቲ የዘንድሮውን የካራባኦ ዋንጫ የማያነሳ ከኾነ የውድድር ዓመቱን ያለዋንጫ ሊያጠናቅቅ ይችላል። ከሻምፒዮንስ ሊግ በማድሪድ ተሸንፎ ወጥቷል። በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ላይ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቢኖረውም ከአርሰናል በዘጠኝ ነጥብ እርቋል። በኤፍ ኤ ካፕ ደግሞ ከሊቨርፑል ከባድ ፈተና ይገጥመዋል።

ማንቸስተር ሲቲ 2025/26 ያለ ዋንጫ የሚያጠናቅቅ ከኾነ ጋርዲዮላ በራሱ ፈቃድ ወይም በክለብ ወሳኔ መልቀቁ አይቀሬ ነው ተብሏል። የቬንገርን ዘመን የቋጨው የ2018 ካራባኦ ዋንጫ ዘንድሮ ደግሞ የፔፕ ተራ ሊኾን ይችላል።

ይህ ዋንጫ ለሁለቱም ክለቦች ወሳኝ ነው። ለአራት ዋንጫዎች እየተጫወተ የሚገኘው አርሰናል የነገውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ለሌሎች ዋንጫዎች ተጨማሪ መነሳሳት ይኾንለታል።

አርሰናል የነገውን ዋንጫ የሚያሳካ ከኾነ ከ34 ዓመታት በኋላ የሚያገኘው የካራባኦ ዋንጫ ይኾናል። ቀጣይ የፕሪምዬር ሊግ እና የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ለማንሳትም ስንቅ ይኾንለታል።

በሌላ በኩል ሲቲ የዋንጫው አሸናፊ የሚኾን ከኾነ ፔፕ ጋርዲዮላ በውድድር ዘመኑ ያለዋንጫ ያጠናቅቁ ይኾን የሚለውን ስጋት ያስቀርላቸዋል። ምን አልባትም ከማንቸስተር ሲቲ ጋርም የሚቀጥሉበት እድል ሰፊ ሊኾን ይችላል።

ለዚህ ነው ታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች አለን ሺረር ከጎል ዶት ኮም ጋር በነበረው ቆይታ “ይህ ዋንጫ ለሁለቱም ክለቦች የውድድር ዓመቱን የሚወስን ነው” ያለው።

አርሰናል በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ባየር ሊቨርኩሰንን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፈበትን ውጤት አስመዝግቦ በመመለሱ የስነ ልቦና የበላይነት ይኖረዋል።

ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሸንፎ እንደ መምጣቱ መጠን በሥነ ልቦና ጫና ሊፈጥርበት ይችላል፤ ነገር ግን ዋንጫ የማንሳት ልምዱን ሊጠቀም ይችላል ተብሏል።

ማንቸስተር ሲቲ እ.አ.አ 2018 እስከ 2021 ድረስ ለተከታታይ 4 ጊዜ ይህንን ዋንጫ አሳክቷል።

አርሰናል ለመጨረሻ ጊዜ ካራባኦ ዋንጫ ያነሳው እ.አ.አ 1993 ሼፊልድ ዊንስዴይን በማሸነፍ ነበር። ከዚህ ዋንጫ በኋላ ለሦስት ጊዜ ለፍጻሜ ቢቀርብም ዋንጫ ማሸነፍ ግን አልቻለም።

በታሪክ ደረጃ አርሰናል የካራባኦ ዋንጫ ያነሳው ለሁለት ጊዜ ብቻ ነው። ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ ከሊቨርፑል ቀጥሎ 8 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት በ2ኛ ደረጃ ተቀምጧል። ሲቲ 9 ጊዜ ለፍጻሜ ቀርቦ ነው ስምንቱን ያሸነፈው።

ነገ ምሽት 1፡30 ላይ በግዙፉ ዌምብሌይ ስታዲየም የሚካሄደውን የካራባኦ ዋንጫ ማን ያሸንፋል? የሚለው በጉጉት ይጠበቃል።

በደሳለው ቢተው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here