ባሕር ዳር: መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ31ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቦርንማውዝ ከማንቸስተር ዩናይትድ ዛሬ ይጫወታሉ። በአሠልጣኝ ማይክል ካሪክ ሥር በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ የዛሬውን ጨዋታ የሚያሸንፍ ከኾነ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ይዞ ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን ፉክክር ያሳምራል።
በቦርንማውዝ ሜዳ በቪታሊቲ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ይጠበቃል።
ቢሶከር በዘገባው ካሪክ በማንቸስተር ዩናይትድ አስደናቂ አጀማመር እንዳሳየ ገልጿል። ማይክል ካሪክ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ተስፋ በጨለመበት ጊዜ ብርሃን ኾኖ የመጣ አሠልጣኝ ነው ብሏል። ካሪክ ክለቡን ከአስከፊ የውጤት ቀውስ አውጥቶ ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ቦታ ፉክክር መልሶታል። የዛሬውን ጨዋታስ አሸንፎ ለሻምፒዮንሰ ሊግ ቦታ ለማግኘት የሚደረገውን ፉክክር ያጠናክራል? የሚለው ይጠበቃል።
ቦርንማውዝ ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ባደረገው የመጨረሻዎቹ አምስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አልተሸነፈም። ሁለት ጊዜ ያሸነፈ ሲኾን ሦስት ጊዜ ደግሞ አቻ መውጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ቦርንማውዞች ያለፉትን አራት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች አቻ ወጥተዋል። ከእነዚህም ውስጥ በሦስቱ ጎብ ማስቆጠር አልቻሉም። ዛሬም በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት በጥሩ አቋም ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታም ፈታኝ እንደሚኾንባቸው ይጠበቃል።
ማይክል ካሪክ ማንቸስተር ዩናይትድን ከተረከበ ጀምሮ በፕሪሚየር ሊጉ የማንቸስተር ዩናይትድን ያክል ያሸነፈ ክለብ የለም። እንደ ማንቸስተር ዩናይትድም በርካታ ነጥቦችን የሰበሰበ ክለብ የለም። ዛሬስ ሙሉ ሦስት ነጥቡ ያሳካል? የሚለው የሚጠበቅ ይኾናል።
ጨዋታው ምሽት 5:00 ላይ ይካሄዳል።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



