ሴኔጋል በጨዋታ፣ ሞሮኮ በቅሬታ ያሸነፉበት የአፍሪካ ዋንጫ።

0
34
ባሕርዳር፡ መጋቢት 10/2018ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ እግር ኳስ አዲስ መነጋገሪያ ርዕስ ተፈጥሯል። የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ተጠናቅቆ ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በሚታሰብበት ጊዜ ካፍ አዲስ ርዕሰ ጉዳይ ይዞ መጥቷል።
የዋንጫውን አሸናፊ ሴኔጋልን ጥፋተኛ ነሽ በማለት ዋንጫውን ነጥቋታል። ዋንጫውንም ለሞሮኮ አሳልፎ ሰጥቷል። የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ ሴኔጋል በጨዋታ፣ ሞሮኮ ደግሞ በቅሬታ ዋንጫ ያሸነፉበት ኾኗል።
ይሄን ውሳኔ ያዩ ደጋፊዎች በታሪክ ረጅም የምስል ዳኝነት ( የቫር) ዕይታ ውሳኔ የተጠበቀበት እያሉ እየጠሩት ነው። ቢቢሲ በዘገባው የ2025 የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ በቅንጡ ስታድየሞች፤ በበርካታ እና ረጅም እርቀት በተጓዙ ደጋፊዎች የደመቀ ነበር ይላል። የአፍሪካ እግር ኳስ በብዙዎች ዘንድ ትኩረት እያገኘ፤ ከጊዜ ወደጊዜም እያደገ ነው። መጨረሻው ግን በውዝግብ ተሞልቷል ይላል።
የ2025 የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት፤ የማይረሱ ሀነቶችም የነበሩበት ነበር። ይህ ደማቅ ውድድር ከሁለት ወራት በፊት ቢጠናቀቅም የውጤት ውሳኔዎች ከወራት በኋላ ታይተውበታል። አሸናፊዋ ሴኔጋል ዋንጫውን ተነጥቃ ለአዘጋጇ ሀገር ሞሮኮ ዋንጫ ተሰጥቷልና።
ቢቢሲ አንድ የእግር ኳስ ደጋፊን አናግሮ ይሄን ክስተት ሲገልጸው በታሪክ ውስጥ ረጅሙ የምስል ዳኝነት (ቫር) ፍተሻ የተካሄደበት ነው ብሏል።
ሞሮኮ በዳኝነት ውሳኔዎች ተጠቃሚ እንደነበረች ትተቻለች የሚለው የቢቢሲ ዘገባ የሞሮኮ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መካከል ካለው የጠበቀ ግንኙነት ጋር የተያያዙ የሴራ ውሳኔዎች እንዳሉ ይገመታል ይላል።
ሞሮኮ በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ጠንካራ ማዕከል ኾናለች። ውድድሮችን ታስተናግዳለች፤ በሜዳቸው መጫወት ለማይችሉ ሀገራት በርካታ የማጣሪያ ጨዋታዎችን በማስተናገድ ካፍን ትረዳለች። ይህም ግንኙነት ሞሮኮ ውሳኔዎች እንዲወሰኑላት ዕድል ሳይሰጥ አልቀረም እየተባለ ሃሜት አለ ነው የሚለው።
በፍጻሜው የታየው የዳኝነት ክፍተት የዳኝነት ውሳኔውን ተከትሎ የተፈጠረው ትርምስ የአፍሪካ ዋንጫው መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር።
በዳኛው ውሳኔ የተበሳጩ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ሜዳውን ለቅቀው እስከ መውጣት ደርሰዋል። ይህም የሴኔጋልን ብሔራዊ ቡድን ሲያስተች ነበር። ጨዋታው በአለመግባባት ተቋርጦ ቆይቷል። በመካከል በተደረገ ውይይት ጨዋታው እንዲቀጥል ተደርጎ ሴኔጋል አሸናፊ ኾናለች።
ካፍም ይሄን ዋንጫ ለሴኔጋል አስረክቧል። ነገር ግን በጨዋታው ላይ ባሳየችው ያልተገባ ባሕሪ ሴኔጋልን ቀጥቶ ነበር። የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድንም በሀገሩ የዋንጫውን ደስታ አክብሯል።
ከወራት በኋላ ግን ሌላ ውሳኔ መጥቷል። ዋንጫውን አሸንፈሻል ብሎ የሽለማት ካፍ አሁን ደግሞ በይግባኝ አላሸነፍሽም ይልቅስ ጥፋተኛ ነሽ ብሎ ዋንጫውን እንደተነጠቀች አስታውቋል።
የአፍሪካ እግርኳስ ባለሙያው ማሄር ሜዛሂ ማንም ሰው ሞሮኮን አሸናፊ አድርጎ የሚቆጠር አይመሰለኝም ይላል። ሴኔጋል ለዓለም አቀፉ የስፖርት የግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) ቅሬታዋን ታቀርባለች፤ ይግባኟ ተቀባይነት እንደሚኖረው እና ሴኔጋል የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ኾና እንደምትቀጥል እንጠብቃለን ነው የሚለው።
የዓለም አቀፉ የስፖርት የግልግል ፍርድ ቤቱ ይህንን ውሳኔ ቢያጸድቅም እንኳ ማንም ሰው ሞሮኮን የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ናት ብሎ ይቆጥራታል ብዬ አላስብም ይላል።
የቀድሞው የካሜሮን ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ሴባስቲን ባሶንግ በውሳኔው በጣም ደንግጫለሁ፤
በዚህ ውሳኔ ትልቁ ተጎጂ የሴኔጋል ተጫዋቾች ወይም የሴኔጋል ሕዝብ አይደለም፤ የሚጎዳው የአፍሪካ እግር ኳስ ነው እንጂ ብሏል።
ሴኔጋል የካፍ ውሳኔን ተከትሎ በካፍ ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች። ውሳኔው ታይቶ የማይታወቅ ነው ያለችው ሴኔጋል በተሳሳተ ትርጓሜ ላይ በመመስረት ሕገወጥ እና ኢ ፍትሐዊ ውሳኔ ተላልፏል ብላለች። ሴኔጋል ይሄን ፍትሐዊ ያልኾነ ውሳኔም እንደምትቃወም አስታውቃለች።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዝዳንት ፓትሪስ ሞትሴፕ (ዶ.ር) በፍፃሜው ጨዋታ ወቅት የተፈጠሩ ክስተቶች የእግር ኳስ ጨዋታዎቻችንን ውጤት ታማኝነት፣ ክብር፣ ሥነ ምግባር እና አሥተዳደርን ለማረጋገጥ የተደረገውን ሥራ አበላሽተዋል ነው ያሉት።
የካፍ የዲሲፕሊን እና የይግባኝ ቦርዱ ውሳኔዎች በታማኝነት መታየት እንዳለባቸውም ገልጸዋል። በአፍሪካ ውስጥ አንድም ሀገር ከሌላው በበለጠ ተመራጭ፣ የበለጠ ጠቃሚ ወይም የተሻለ በኾነ መንገድ አይስተናገድም ብለዋል።
የካፍ ውሳኔ ይጸናል ወይስ የዓለም አቀፉ የስፖርት የግልግል ፍርድ ቤት (ካስ) ውሳኔውን ሽሮ ሴኔጋል የዋንጫ አሸናፊ እንደኾነች እንድትቀጥል ያደርጋል? የሚለው ውጤት ይጠበቃል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here