በ24 ሰዓታት ውስጥ አራት የእንግሊዝ ክለቦች የተሰናበቱበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ።

0
53
ባሕርዳር፡ መጋቢት 10/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ትናንት እና ከትናንት ወዲያ ተካሂደዋል። ስምንት ክለቦች ወደ ሩብ ፍጻሜው ሲቀላቀሉ ስምንት ክለቦች ደግሞ ከውድድሩ ተሰናብተዋል።
ከተሰናበቱት ስምንት ክለቦች መካከል አራቱ ደግሞ የእንግሊዝ ክለቦች ናቸው። ቢቢሲ በዘገባው በ24 ሰዓታት ውስጥ አራት የእንግሊዝ ክለቦች ከውድድሩ ተሰናብተዋል ብሏል።
ከትናንት ወዲያ በተካሄዱ ጨዋታዎች ቸልሲ በፒኤስ ጂ በሰፊ የግብ ልዩነት ተሸንፎ ከውድድሩ ተሰናብቷል። ማንቸስተር ሲቲም በመድረኩ ንጉሥ ሪያል ማድሪድ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ኾኗል።
ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ኒውካስትል ዩናይትድ በባርሴሎና በሰፊ የግብ ልዩነት ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ኾኗል። በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐርስም በአትሌቲኮ ማድሪድ ተሸንፎ ተሰናብቷል።
በ24 ሰዓታት ውስጥ ለተሰናበቱት አራቱ የእንግሊዝ ክለቦች ሦሥቱ የተሸነፉት በስፔን ክለቦች ነው። ቢቢሲ በዘገባው በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የነበሩ ስድስቱ የእንግሊዝ ክለቦች ሁሉም ወደ ጥሎ ማለፍ ተሸጋግረው ነበር።
ነገር ግን ወደ ሩብ ፍጻሜው ለማለፍ በተደረገው ፍልሚያ የቀሩት ሁለቱ ብቻ ናቸው፤ አርሰናል እና ሊቨርፑል። አራቱ ግን በጊዜ ተሸኝተዋል።
ቢቢሲ በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ እና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች የአጨዋወት ልዩነት እንዳለ ጽፏል። በሊጉ ከባድ ፉክክር የሚያደርጉት የእንግሊዝ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተቸግረው ታይተዋል።
ክለቦቹ ከውድድሩ በጊዜ እንዲሰናበቱ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል ተደራራቢ ጨዋታዎች መብዛት፣ ጉዳቶች እና የተጫዋቾች እረፍት ማጣት እንደኾነ ተገልጿል።
ተደራራቢ የጨዋታ ጊዜ መኖር ተጫዋቾችን እንደሚጎዳ እና በውድድር ውጤታማ እንደማያደርጋቸው አሠልጣኞች በተደጋጋሚ ይናገሩት እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል። ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የተሰናበቱት የእንግሊዝ አራቱ ክለቦች በደርሶ መልስ ሁሉም ከአምስት በላይ ግቦች ተቆጥረውባቸዋል።
በእንግሊዝ ክለቦች ያለው የጨዋታ መደራረብ እና የተጫዋቾች እረፍት ማጣት ወደፊትም እንደሚፈትን አሠልጣኞች በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ይሄም ስጋት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ታይቷል።
በአንጻሩ የፈረንሳይ፣ የጀርመን እና የስፔን ሊጎች ላይ በቂ እረፍቶች እንዳሉ ቢቢሲ ዘግቧል። በዚህ የውድድር ዘመን የፕሪምዬር ሊግ ክለቦች በተለይም አሁንም በዋንጫ ውድድሮች ላይ የሚገኙት ክለቦች በመላው አውሮፓ ካሉ ሌሎች ክለቦች በበለጠ ብዙ ጨዋታዎችን ተጫውተዋል።
በርካታ ጨዋታዎች ማድረግ ደግሞ ለተጫዋቾች ጉዳት አና ድካም እያጋለጠ ነው። በፕሪምዬር ሊጉ ያለው ጠንካራ ፉክክርም የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ክለቦች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ደክመው እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል።
በሌሎች ሊጎች ያለው ቀለል ያለ ፉክክር ታላላቅ ተጫዋቾች ዝቅተኛ ግምት በሚሰጣቸው ጨዋታዎች ያርፋሉ። ለአህጉራዊ ውድድር ደግሞ በበቂ እረፍት እና በተሻለ አቋም ይመለሳሉ።
በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ ግን ያለው ብርቱ ፉክክር ለተጫዋቾች እረፍት እንዳይሰጥ አድርጓል ይላል ቢቢሲ። ከባድ እና አድካሚ ፉክክር የሚደረገበት የእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ አራት ክለቦችም በጊዜ ከውድድሩ ወጥተዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here