አርሰናል እና አርቴታ፤ የአዲስ ታሪክ ጨዋታ

0
103
ባሕር ዳር: መጋቢት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ የእግር ኳስ ከዋክብት ለአንድ ክለብ በተጨዋችነታቸው እና በአሠልጣኝነታቸው የተለያዩ ስኬቶችን አስመዝግበዋል፤ ለዚህም በአብነት የሚጠቀሱ አሉ።
ካርሎ አንቼሎቲ የኤስ ሚላን ተጨዋች በነበሩበት ወቅት በአሠልጣኝ አሪጎ ሳኪ እየተመሩ ከጣሊያኑ ክለብ ኤስ ሚላን ጋር የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ዋንጫን፣ የአውሮፓ ሱፐር ካፕን፣ የጣሊያን ሴሪ ኤን እና የጣሊያን ሱፐር ካፕን አሸንፈዋል፡፡
የቶታል ፉት ቦል መሥራች እየተባሉ የሚወደሱት ኔዘርላንዳዊው ዮሃን ክራይፍም ከኔዘርላንድሱ አያክስ አምስተርዳም እና ከስፔኑ ባርሴሎና ጋር በተጨዋችነት እንዲኹም በአሠልጣኝነት በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበዋል፡፡
ከአያክስ ጋር ስምንት የኔዘርላንድስ ሊግ (ኤር ዲቪዝ)፣ ሦስት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ዋንጫን በተጨዋችነታቸው አሳክተዋል፡፡ ከባርሴሎና ጋርም አንድ የላሊጋ ዋንጫ እና አንድ የስፔን የንጉሥ ዋንጫን (ኮፓ ዴላሬ) አሸንፈዋል፡፡
ዮሃን ክራይፍ በእነዚህ የተጨዋችነታቸው ዘመናት ሦስት ጊዜ የባላንዶር አሸናፊ ኾነው ተመርጠዋል፡፡
በባርሴሎና አሠልጣኝነታቸው ደግሞ አራት የላሊጋ ዋንጫዎችን ጨምሮ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ሌሎች በርካታ ዋንጫዎችንም አሳክተዋል፡፡
ፍራንዝ ቤከንባወር በባየር ሙኒክ በተጨዋችነት እና በአሠልጣኝነት ውጤታማ የኾኑ ሰው ናቸው፡፡
ኬኒ ዳግሊሽም በሊቨርፑል በተጨዋችነት እና በአሠልጣኝነት ጥሩ ውጤት ካስመዘገቡት ውስጥ ይመደባሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜዎቹ ደግሞ ፔፕ ጋርዲዮላ በስፔኑ ባርሴሎና ክለብ በተጨዋችነት እና በአሠልጣኝነት ዋንጫዎችን አሳክተዋል፡፡
ፈረንሳዊው ዚነዲን ዚዳንም በሪያል ማድሪድ በተጨዋችነት እና በአሠልጣኝነት ከተሳካላቸው እግር ኳሰኞች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡
ስፔናዊው የአርሰናል አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ምንም እንኳን በአርሰናል የተጨዋችነታቸው ጊዜ ሁለት የኤፍ ኤ ዋንጫን ከማሸነፍ የዘለለ ደማቅ ታሪክ ባይኖራቸውም ዘንድሮ በአርሰናል አሠልጣኝነታቸው ለአራት ዋንጫዎች እየተፋለሙ ለአዲስ ታሪክ በአዲስ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሚኬል አርቴታ አርሰናል በታሪኩ አሳክቶት የማያውቀውን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ጨምሮ ለ22 ዓመታት ማሳካት ያልቻለውን የፕሪምዬር ሊግ ዋንጫ ያሳኩ ዘንድ የብዙ ደጋፊዎች ምኞት ነው፡፡
ሚኬል አርቴታ አርሰናልን ባሠለጠኑባቸው ያለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ማሳካት የቻሉት አንድ የኤፍ ኤ ክፕን ዋንጫ ብቻ ነው። ዘንድሮ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ ውስጥ፤ በእንግሊዝ ፕሪምዬር ሊግ እስከ 29ኛው ሳምንት ከተከታዩ ማንቸስተር ሲቲ በሰባት ነጥቦች በልጦ ይገኛል፡፡
አርሰናል በኤፍ ኤ ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው ከሳውዝ አምፕተን ጋር የሚጫወት ሲኾን በካራባው ካፕ ደግሞ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ለዋንጫ ይፋለማል፡፡
አርሰናል እና አሠልጣኙ ሚኬል አርቴታ የትኞቹን ዋንጫዎች ያሳኩ ይኾን?
ዘጋቢ፡- እሱባለው ይርጋ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here