ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየሠራ መኾኑን የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

0
41

 

ፍኖተሰላም፡ መጋቢት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን በስፖርት እንዲያሳልፉ እና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን አስታውቋል።

በከተማዋ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የ”ኤምዋይዜድ” ስፖርት ፕሮጀክት አንዱ ነው። በሥልጠና ማዕከሉ የታቀፉ ወጣት ተጫዋቾች ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናቸውን በሚገባ በመከታተል እና በተለያዩ ውድድሮች በመሳተፍ ውጤታማ እየኾኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ከከተማ ውድድሮች ባለፈ በከፍተኛ ሊግ እና በኢትዮጵያ ፕሪምዬር ሊግ ውስጥ ተጫዋች የመኾን ራዕይ ሰንቀው እየሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ አሠልጣኝ ዘላለም አንሙት ፕሮጀክቱ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱን አንስተዋል። ተጫዋቾች በሥነ ልቦና እና በአካል ብቁ እንዲኾኑ በሳምንት ሦሥት ቀናት ሥልጠና ይሰጣል ነው ያሉት።

ይህም ወጣቶች በትርፍ ሰዓታቸው ጤናማ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ ከማድረጉ ባለፈ በተለያዩ ክለቦች ውስጥ ተሳታፊ እንዲኾኑ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን አስረድተዋል።

የቡድኑ መሪው ታደለ ደጉ ስፖርቱን ለማሳደግ የኅብረተሰቡ እና የባለሀብቶች ድጋፍ ወሳኝ መኾኑን ጠቁመዋል። የግብዓት እና የማዘውተሪያ ስፍራ እጥረት ፈተና እየኾነባቸው መኾኑን ገልጸዋል።

የፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የስፖርት ዘርፍ ቡድን መሪ ዘላለም ደምሴ የ”ዳሞት ከነማ” የእግር ኳስ ክለብ ወደ ውድድር ሲመለስ ተተኪ ተጫዋቾችን ለማግኘት የሥልጠና ማዕከላትን የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በተለይም ወጣቶች ጤናማ እንዲኾኑ እና ራሳቸውን ከማይፈለጉ ድርጊቶች እንዲጠብቁ ስፖርት ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ እንቅፋት የኾኑትን የግብዓት እና የማዘውተሪያ ቦታ ችግሮችን ለመፍታት ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ብቁ ስፖርተኞችን ለማፍራት ሁሉም አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here