በሰቆጣ ከተማ የ8 ኪሎ ሜትር የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ።

0
42

 

ሰቆጣ: የካቲት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመልከት በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ በተካሄደ የ8 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በርካታ ሴቶች ተሳትፈዋል።

ውድድሩ የታዳጊዎችን አቅም ለማውጣት እና ስፖርቱን ለማነቃቃት ያለመ ነው።

ውድድሩን በአንደኝነት ያጠናቀቀችው ተማሪ መቅደስ አለነ መድረኩ ቀደም ሲል የመወዳደር ዕድል ላላገኙ ታዳጊዎች ትልቅ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጻለች።

በሁለተኛነት ያጠናቀቀችው ተማሪ ምሥራቅ ቢራራ በበኩሏ ውድድሩ በአትሌቲክሱ ዘርፍ እንድትቀጥል በር የከፈተላት መኾኑን እና በቀጣይ በዞን ደረጃ ለሚደረጉ ውድድሮች በርትታ እንደምትዘጋጅ ተናግራለች።

የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ትበርህ ታደሰ ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ አሳታፊ ያደረገች ሀገር ውጤታማ እንደምትኾን ገልጸዋል።

በቀጣይም የአደባባይ ስፖርቶች ሴቶችን ማዕከል አድርገው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ቡድን መሪ አበራ ቢምረው ውድድሩ እየተቀዛቀዘ የመጣውን አትሌቲክስ ለማነቃቃት ፋይዳው የጎላ መኾኑን ጠቁመዋል።

ተቋማት ተቀራርበው መሥራታቸው ለስፖርቱ ዕድገት ዋጋ እንዳለው እና በታዳጊዎች ላይ በትኩረት ለመሥራት መታቀዱንም አክለዋል።

በውድድሩ አሸናፊ ለኾኑ አትሌቶች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here