በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ዋንጫ ዛሬ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

0
66

 

ባሕርዳር: የካቲት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማንችስተር ሲቲ ከኒውካስትል፣ አርሰናል ከማንስፊልድ ታውን እና ቼልሲ ከሬክሳም በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ዋንጫ 5ኛ ዙር ዛሬ የሚጠበቁ ጨዋታዎች ናቸው። አራቱንም ዋንጫዎች የማንሳት ተስፋ የሰነቁት ማንችስተር ሲቲ እና አርሰናል ሩብ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ኒውካስትል ዩናይትድ ከ ማንችስተር ሲቲ ምሽት 5:00 የሚያደርጉት ጨዋታ የዕለቱ ታላቅ ጨዋታ ነው።

በሴንት ጄምስ ፓርክ ስታዲየም በኒውካስትል እና በማንችስተር ሲቲ መካከል የሚደረገው ይህ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የውድድር ዓመት ብቻ ለ5ኛ ጊዜ የሚገናኙበት ነው።

ሲቲ በቅርቡ በካራባኦ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ኒውካስትልን በደርሶ መልስ አሸንፎ ለፍፃሜ መድረሱ ይታወሳል።

በማንችስተር ሲቲ በኩል ጆስኮ ግቫርዲዮል እና ማቲዮ ኮቫቺች በጉዳት የማይሰለፉ ሲኾን የኒኮ ኦሪሊ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። በኒውካስትል በኩል ጃኮብ ራምሴ በቅጣት አይሰለፍም።

ሁለቱ ቡድኖች በኤፍ ኤ ዋንጫ ታሪካቸው ለ11ኛ ጊዜ ይገናኛሉ።

ሌላው ጨዋታ ማንስፊልድ ታውን ከአርሰናል ቀን 9:15 የሚገናኙበት ጨዋታ ነው።

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን በ7 ነጥብ ልዩነት እየመሩ የሚገኙት መድፈኞቹ፣ በ3ኛው የሊግ እርከን ከሚገኘው ማንስፊልድ ታውን ጋር ከሜዳቸው ውጭ ይጫወታሉ።

አሠልጣኝ ሚካኤል አርቴታ በሊጉ ብራይተንን ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ በርካታ ለውጦችን እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

አርሰናል በኤፍ ኤ ዋንጫ ከታችኛው ሊግ ቡድኖች ጋር ያደረጋቸውን ያለፉትን 15 ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፏል። ይህ ጨዋታ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ከ95 ዓመታት በኋላ የሚደረግ የመጀመሪያው የኤፍ ኤ ዋንጫ ግንኙነት ይኾናል።

ቼልሲ ከሬክሳም ምሽት 2:45 የሚደረግ ሌላው ተጠባቂ ጨዋታ ነው።

በሳምንቱ አጋማሽ አስቶን ቪላን 4ለ1 በማሸነፍ በራስ መተማመኑ የተመለሰው ቼልሲ የሆሊውድ ኮከቦች ባለቤት ከኾኑበት ሬክሳም ጋር ይጫወታል።

ዓመቱን ያለ ዋንጫ ማጠናቀቅ የማይፈልገው ቼልሲ ሩብ ፍፃሜውን ለመቀላቀል ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here