ኢራን በ2026 የዓለም ዋንጫ ትሳተፍ ይኾን ?

0
76

 

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የ2026 የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በሜክሲኮ አዘጋጅነት እ.ኤ.አ ከሰኔ 11 እስከ ሐምሌ 19/2026 ድረስ ይካሄዳል።

ፊፋ በታኅሣሥ ወር 2026 ባካሄደው የተሳታፊ ሀገራት እጣ ማውጣት ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕን የመጀመርያው የፊፋ የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ማድረጉ ይታዎሳል። ትራምፕም በሥነ ሥርዓቱ ላይ የ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ያለምንም ኮሽታ እንዲካሄድ አሜሪካ ትሠራለች ብለው ነበር።

ከሰሞኑ አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር ግጭት ውስጥ ገብተዋል። ይህ ግጭት ደግሞ ከፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተጽዕኖው ባሸገር በስፖርቱ ላይ ጥላውን እንዳያጠላ ተሰግቷል።

ኢራን በ2026 የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ከሚኾኑ 48 ሀገራት አንዷ ናት። የዓለም የመገናኛ ብዙኃን ታዲያ ሊካሄድ 99 ቀናት በቀሩት የዓለም ዋንጫ የኢራን ቡድን በአሜሪካ ምድር ተገኝቶ ይሳተፍ ይኾን ? እያሉ ነው። እንሳተፍ ቢሉስ የደኅንነት ዋስትና ይኖራቸዋል ? የሚለው ጉዳይ አነጋገር ነው።

ምንም እንኳን ውድድሩን ፊፋ በበላይነት ቢመራውም ኢራን ጠላት በምትላት ሀገር ትጫወታለች የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ነው።

ቢቢሲ ዛሬ ባወጣው መረጃ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በዓለም ዋንጫ ላይ ብትጫወት ግድ እንደሌላቸው መናገራቸውን ዘግቧል። ፕሬዝዳንቱ “ኢራን በውድድሩ ላይ ብትሳተፍ በእርግጥም ግድ የለኝም” ነው ያሉት።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተከሰተው ከባድ ውዥንብር የኢራን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ መህዲ ታጅ በተሳትፎአቸው ላይ ጥርጣሬ እንዳሳደሩ ተዘግቧል።

ታጅ ለኢራን ቴሌቪዥን እንደተናገሩት የዓለም ዋንጫን በተስፋ መመልከት እንደሚቻል አንስተዋል። የሀገሪቱ የስፖርት ባለሥልጣናት ማንኛውም እርምጃ አስፈላጊ ከኾነ ይወስናሉም ብለዋል።

የፊፋ ዋና ፀሐፊ ማቲያስ ግራፍስትሮም ባለፈው ቅዳሜ በሰጡት አስተያየት ትኩረታችን ሁሉም የሚሳተፍበት ደኅንነቱ የተጠበቀ የዓለም ዋንጫ እንዲኖር ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በሙሉጌታ ሙጨ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here