ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በስፔን ላ ሊጋ ዛሬ ምሽት 5:00 ሪያል ማድሪድ በሜዳው ስታዲዮ ሳንቲያጎ ቤርናባው ጌታፌን የሚጋብዝበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ሪያል ማድሪድ ከ25 ጨዋታዎች 60 ነጥብ በመሠብሠብ ከመሪው ባርሴሎና በአራት ነጥብ ልዩነት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አንድ ማጥበብ ያስችለዋል።
የሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ አልቫሮ አርቤሎዖ ለጨዋታው እንደ ሮድሪጎ ያሉ ወሳኝ ተጫዋቾች ዝግጁ ናቸው ብለዋል። በተለይ ሮድሪጎ ከቀኝ እና ግራ ክንፍ እንዲሁም ከፊት መስመር ኳስን ወደ ሳጥን በማድረስ የአንድ ብዙ ተጫዋች ነው በማለት በተጫዋቹ መሠለፍ መደሰታቸውን አልሸሸጉም።
“ተጫዋቾቼ በጥሩ ጨዋታ ጥሩ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ አልጠራጠርም” ማለታቸውን ጎል ዶት ኮም አስነብቧል።
ተጋጣሚው ጌታፌ ደግሞ ከ25 ጨዋታዎች 29 ነጥብ ብቻ በመያዝ 14ኛ ላይ ተቀምጧል። በጨዋታው የሚያሸንፍ ከኾነ ነጥቡን 32 በማድረስ ሦሥት ደረጃ የሚያሻሽል ይኾናል።
የጌታፌ አሠልጣኝ ጆሴ ቦርዳላዝ የምንጫወተው ሪያል ማድሪድን እያሰብን ሳይኾን ለማሸነፍ በመኾኑ ጥሩ ውጤት እናስመዘግባለን የሚል ተስፋ አለኝ ነው ያሉት።
ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2004 ወዲህ በ42 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ሪያል ማድሪድ በ32 ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው።
ጌታፌ ያሸነፈው በስድስት ጨዋታዎች ብቻ ሲኾን በአራት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በተለይ በሳንቲያጎ ቤርናባው ስታዲየም ጌታፌ ድል የቀናው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው።
ላ ሊጋውን ባርሴሎና ሲመራው ሪያል ማድሪድ ይከተለዋል። አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ በሦሥተኛነት ይከተላል።
በላሊጋው ማዮርካ፣ ሌቫንቴ እና ሪያል ኦቢዶ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



