ባሕር ዳር: የካቲት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሪያል ማድሪድ እና ቤኔፊካን ያገናኘው ጨዋታ ትኩሳት አሁንም ቀጥሏል። ምክንያቱ ደግሞ በብራዚላዊው የሪያል ማድሪድ ተጫዋች የደረሰው ዘር ተኮር ጥቃት ነው።
የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ቪኒሽየስ ጁኔር ደስታውን ሲገልጽ የቤኔፊካ ደጋፊዎች ቁሳቁሶችን ወደ ተጫዋቹ ወረወሩ። ከዚህ አልፈውም የቆዳ ቀለሙን መሠረት ያደረገ ጥቃትን አስከተሉ።
የዕለቱ የመሀል ዳኛ እጃቸውን አጣምረው በማሳየት የዘረኝነት ጥቃት ተጫዋቹ ላይ እየደረሰ ነው ብለው በማወጅ ጨዋታውን በፊሽካ አቋረጡ።
ጨዋታውን መልሶ ለመጀመርም ከ10 ያላነሱ ደቂቃዎች አስፈልገዋል። ከደጋፊዎች በተጨማሪ አርጀንቲናዊው የቤኔፊካ ተጫዋች ፕሪስቲያኒ የዘረኝነት ጥቃት ቪኒሽየስ ላይ ማድረሱን የማድሪድ ተጫዋቾች ለዕለቱ ዳኛ ሪፖርት አድረገዋል።
መሰል ድርጊቶች በዘመኑ የአውሮፓ ሜዳዎች እና ማሠልጠኛዎች ከእኛ በላይ በሚሉት ምዕራባዊያን አዲስ አይደለም። ከዚህ በፊት በርካታ ጥቁር ተጫዋቾች በሙዝ ሲደበደቡ፣ ሜዳ ውስጥ የሚሰነዘርባቸውን አጥንት የሚሰረስር ዘለፋ መቋቋም ተስኗቸው እያነቡ ሜዳ ጥለው ሲወጡ ዓለም ታዝቧል። ጥያቄው ግን ብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሽየስ ላይ ለምን ይበረታል የሚለው ነው?
ተጫዋቹ ከሌሎች ጥቁር ተጫዋቾች በላይ በቅርብ ዓመታት የዘረኞች ትኩረት ኾኗል። ከትናንቱ ክስተት በኋላ ጆዜ ሞሪንሆ ቪኒሽየስ ደጋፊዎችን ላልተገባ ድርጊት አነሳስቷል ብለዋል።
ያን የመሰለ ምርጥ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች የተጋጣሚ ደጋፊን የሚያበሳጭ የደስታ አገላለጽ መጠቀም አልነበረበትም ነው ያሉት። ለቢቢሲ ስፖርት ችግር አለ ያሉት ሞሪንሆ ቪኒሽየስ በሚጫወትባቸው ሜዳዎች ሁሉ ተመሳሳይ ነገር ይፈጠራል ብለው ተጫዋቹ ለሚደርስበት ጥቃት ክብሪት እንደሚያቀብል ገልጸዋል።
እንደ ሞሪንሆ ሁሉ ብራዚላዊ ኮከብ ሜዳ ላይ ለተቃራኒ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች የሚያሳያቸው ድርጊቶች በዚህም ዘመን ጥቁርነትን መቀበል ለሚያቅራቸው ዘረኞች መንገድ መሪ ብለው የሚተቹት ጥቂት አይደሉም።
በተቃራኒው ደግሞ መሰል ምክንያቶች ጉዳዩን ለማድበስበስ እና ተጠያቂነትን ላለማምጣት የሚሰነዘሩ ናቸው ባዮችም አሉ። የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች ዋልኮት የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ከምክንያት ያለፈ ጠንከር ያለ ርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ጆዜ ሞሪንሆን የሚያክል በእግር ኳስ የደመቀ ሰው ለዘረኝነት ሰበብ መስጠትም ልክ አይደለም ብሏል።
ሌላኛው ሃሳብ የሰጠው ቴሪ ሄንሪም በጨዋታ ዘመኑ የገጠሙትን የዘረኝነት ዘለፋዎች በማስታወስ የሚፈጥረውን ከባድ ስሜት አስታውሷል።
በእንዲህ አይነት ጊዜ ሜዳ ውስጥ ብቸኝነት ይሰማሃል ብሏል። ጠንከር ያሉ ርምጃዎች እንደሚያስፈልጉም አንስቷል።
የአውሮፖ እግር ኳስ ማኅበር የትናንቱን ክስተት መርምሮ የሚወስደው እርምት ይጠበቃል። ሪያል ማድሪድ እና ቤኔፊካም የመልስ ጨዋታቸውን ቀጣይ ሳምንት ቤርናቦ ላይ ያደርጋሉ።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን



