በዓለም አቀፍ መድረክ ሀገሩን ለመወከል የሚያልመው ታዳጊ።

0
35
አዲስ አበባ: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የውኃ ዋና ስፖርት ስሟ በጉልህ የሚነሳው የብርሃን ደመቀ ታናሽ ወንድም የኾነው ታዳጊ ናሆም ደመቀ በአዳማ ከተማ በተከናወነው የታዳጊዎች ምዘና ውድድር በዘጠኝ የወርቅ ሜዳሊያዎች ደምቆ ተገኝቷል።
መነሻውን ኮምቦልቻ ያደረገው እና ገና የ13 ዓመት ታዳጊ የኾነው ናሆም ደመቀ ለስኬቱ ምስጢር እህቶቹ በተለይም ብርሃን ደመቀ እንደኾነች ገልጿል። “የእርሷ ጥንካሬ ለእኔ ብርታት ኾኖኛል” የሚለው ናሆም በአዳማው ውድድር ላይ ያሳየው የበላይነት የአማራ ክልልን የውኃ ዋና ስፖርት ከፍታ ያሳየ እንደነበር ተናግሯል።
ታዳጊው ለስኬቱ አስተዋጽኦ ላደረጉት አሠልጣኙ፣ ቤተሰቡ፣ ለኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ እና ለኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምሥጋና አቅርቧል።
የአማራ ክልል ውኃ ዋና አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ኢስማኤል ሙሐመድ ናሆም ጎበዝ ዋናተኛ ብቻ ሳይኾን ለሌሎች ታዳጊዎችም አርዓያ የሚኾን ስፖርተኛ ነው ብለዋል።
በአዳማው ውድድር ክልሉ ውጤታማ እንዲኾን ናሆም እና ጓደኞቹ ያሳዩት ጀግንነት የሚደነቅ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የአማራ ክልል ውኃ ዋና ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሃብታሙ አለባቸው በበኩላቸው ክልሉ በውድድሩ የነበረውን ሀገራዊ የበላይነት ማስቀጠሉን ገልጸው በቀጣይም እንደ ናሆም ያሉ ባለተሰጥኦዎችን ለማብቃት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
ናሆም ደመቀ እንደ እህቱ ብርሃን ደመቀ እና እንደ ተሚክን ጌታቸው ሁሉ ሀገሩን በዓለም አቀፍ መድረክ ወክሎ የመቅዘፍ ትልቅ ሕልም አለው።
ይህንንም ለማሳካት በክልሉ ተጨማሪ ክለቦች እንዲቋቋሙ እና ያሉትንም ማጠናከር እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ኀይለኢየሱስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here