ባሕር ዳር: የካቲት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በስፔን ላሊጋ እና በጣልያን ሴሪኤ ዛሬ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በላሊጋው 23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት 5:00 ቪላሪያል ከእስፓኞል ይጫወታሉ።
ቪላሪያል ከ21 ጨዋታዎች 42 ነጥብ በመሠብሠብ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። እስፓኞል ደግሞ ከ22 ጨዋታዎች 34 ነጥብ በመያዝ ደረጃው ስድስተኛ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በተገናኙባቸው 59 የላሊጋ ጨዋታዎች ቪላሪያል በ39 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይ ነው።
ቪላሪያል የዛሬውን ጨዋታ እና በቀጣይ የሚያደርገውን ተስተካካይ ጨዋታ የሚያሸንፍ ከኾነ የሦሥተኛነት ደረጃን ከአትሌቲኮ ማድሪድ ይረከባል። በመኾኑም ዛሬ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
እስፓኞል ቪላሪያልን ያሸነፈው በአምስት ጨዋታዎች ብቻ ነው። በ15 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የዛሬውን ጨዋታ ያሸነፈ ቡድን የደረጃ ለውጥ ባያገኝም ከኋላ የሚከተለውን ቡድን በነጥብ መራቅ ያስችለዋል።
ላሊጋውን ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ በቅደም ተከተል ይመሩታል።
በጣልያን ሴሪኤ ደግሞ በ24ኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አታላንታ 15ኛ ላይ ከሚገኘው ክሬሞንሴ ምሽት 2:30 ይጫወታሉ።
ሁለቱ ቡድኖች በሴሪኤው በሦሥት ጨዋታ ተገናኝተው አታላንታ በአንዱ ሲያሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል።
በሌላ ጨዋታ ምሽት 4:45 ሮማ ከካግሊያሪ ይጫወታሉ። ካግሊያሪ ጨዋታውን ካሸነፈ አንድ ደረጃ የሚያሻሽል ይኾናል።
ሴሪኤውን ኢንተር ሚላን ይመራዋል። ኤሲ ሚላን ደግሞ በሁለተኛነት ይከተላል። ናፖሊ በሦሥተኛነት ተቀምጧል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



