በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የደረጃ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ጨዋታዎች

0
8
ባሕር ዳር: ጥር 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በዛሬው የ25ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሰባት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
በተለይም ቀን 9:30 ሰዓት ላይ ማንቸስተር ዩናይትድ በኦልድ ትራፎርድ ቶትንሃምን የሚጋብዝበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ ከ24 ጨዋታዎች በ41 ነጥቦችን በመሰብሰብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ቡድኑ አምስተኛ ላይ ኾኖ ከሚከተለው ቼልሲ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት አንድ ብቻ ነው። እናም ተከታዩ ቼልሲ ደረጃውን እንዳያስለቅቀው ዛሬ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
ተጋጣሚው ቶትንሃም በ29 ነጥብ 14ኛ ደረጃን የያዘ ሲኾን ጨዋታውን ካሸነፈም አንድ ደረጃ ያሻሽላል።
ምሽት 12:00 ሰዓት ላይ ደግሞ ቦርንማውዝ በሜዳው ቪታሊቲ ስታዲየም ከአስቶንቪላ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።
አስቶንቪላ ከ24 ጨዋታዎች 46 ነጥብ በመሠብሠብ በሦስተኛነት ተቀምጧል።
ቡድኑ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ብቻ ነጥቡን 49 በማድረስ የሁለተኛ ደረጃን ከማንቸስተር ሲቲ የሚረከብ ይኾናል።
ተጋጣሚው ቦርንማውዝ ደግሞ በ33 ነጥብ 12ኛ ላይ ይገኛል። በጨዋታው ድል መንሳት ደረጃውን ከፍ ማድረግ ስለሚያስችለው አስቶንቪላን ይፈትነዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ከ2015 ወዲህ በ11 የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ተገናኝተው አስቶን ቪላ በአምስት ጨዋታዎች አሸንፏል። ቦርንማውዝ ደግሞ በአራት ጨዋታዎች ነው ድል ማድረግ የቻለው። በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ዛሬስ? ምሽት 12:00 ሰዓት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ምላሹን ይሰጠናል። በተመሳሳይ ምሽት 12:00 ሰዓት ላይ ዎልቭስ ከቼልሲ ይጫወታሉ።
ማንቸስተር ዩናይትድ ነጥብ ከጣለ እና ቼልሲ ወልቭስን ካሸነፈ ቼልሲ የአራተኛ ደረጃን ከቀያይ ሰይጣናቱ ይረከባል። በመኾኑም ቼልሲ እና ወልቭስ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶትንሃም የሚያደርጉት ጨዋታ አጓጊ እና ተጠባቂ ኾኗል።
በሌሎች የምሽት 12:00 ሰዓት ጨዋታዎች፦
👉 አርሰናል ከሰንደርላንድ
👉 በርንሌይ ከዌስትሃም
👉 ፉልሃም ከኤቨርተን ይጫወታሉ።
ምሽት 2:30 ሰዓት ላይ ደግሞ ኒውካስትል ከብሬንት ፎርድ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሊጉን አርሰናል በ53 ነጥብ ይመረዋል። ማንቸስተር ሲቲ በ47 ነጥብ በሁለተኛነት ተቀምጧል። አስቶንቪላ በ46 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
ዌስትሃም፣ በርንሌይ እና ወልቭስ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ይገኛሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here