ፋሲል ከኢትዮጵያ መድን፣ ባሕር ዳር ደግሞ ከንግድ ባንክ ይጫወታሉ።

0
29
ባሕር ዳር፡ ጥር 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሲቢኢ የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም በአዲስ አበባ እንዲሁም በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየሞች ቀጥለው ይውላሉ።
ፋሲል ከነማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከኢትዮጵያ መድን ጋር ቀን 7:00 የሚያደርገው ጨዋታ ደግሞ ጥሩ ፉክክር እንደሚታይበት ይጠበቃል።
አጼዎቹ እስካሁን ካደረጓቸው 17 ጨዋታዎች በስምንቱ በማሸነፍ፣ በስምንቱ አቻ በመለያየት እና በአንዱ በመሸነፍ 32 ነጥብ በመያዝ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ባለፈው ሳምንት የቅዱስ ጊዮርጊሱ በተጠባቂ መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ማሸነፉ ይታወሳል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን ከ18 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአራቱ ብቻ ነው። በሰባቱ አቻ በመለያየት በሰባቱ በመሸነፍ 19 ነጥብ በመያዝ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቡድኑ ወራጅ ቀጣናው አፋፍ ላይ በመኾኑ ዛሬ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ይጫወታል።
በዚሁ አዲስ አበባ ስታዲየም ቀን 10:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ይገጥማል።
ፈረሰኞቹ ከ18 ጨዋታዎች 23 ነጥብ በመያዝ ስምንተኛ ናቸው። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ከ18 ጨዋታዎች16 ነጥብ በመያዝ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ 19ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ደግሞ ባሕር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀን 9:00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የጣናው ሞገድ ከ18 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአራቱ ብቻ ነው። በ11 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። የተሸነፈው በሦሥት ጨዋታዎች ነው።
23 ነጥብ በመያዝም ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የባሕር ዳር ከተማ ደጋፊዎቹ ቡድኑ ለ11ኛ ጊዜ ያስመዘገበውን የአቻ ውጤት ቀልብሶ ወደ አሸናፊነት እንዲመለስ ጉጉታቸው ከፍተኛ ነው።
ቡድኑ ያለበትን 90 ደቂቃ ሙሉ የማጥቃት ውስንነት እና የመልሶ ማጥቃት ወረራ ችግርን ማስወገድ ይኖርበታል።
ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ18 ጨዋታዎች ያሸነፈው በተመሳሳይ በአራት አጋጣሚ ነው። በስምንቱ ተሸንፎ እና በስምንቱ አቻ ወጥቶ 20 ነጥብ በመያዝ 12ኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መረጃ መሰረት ምሽት 12:00 ደግሞ አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ እና መቀሌ 70 እንደርታ የሚጫወቱ ይኾናሉ።
ነገሌ አርሲ ከ18 ጨዋታዎች በ32 ነጥብ የሦሥተኛ ቦታን ይዞ ነው የሚገኘው።
መቀሌ 70 እንደርታ በበኩሉ በ18 ነጥብ ወራጅ ቀጣናው ውስጥ 17ኛ ነው። የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈም ከወራጅ ቀጣናው መውጣት ይችላል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here