ባሕርዳር፡ ጥር26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ከጨዋታ ፉክክርነቱ ባሻገር ዳጎስ ያለ ገቢ የሚያስገኝ የውድድር መድረክ ነው፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ከመጀመሪያው ምዕራፍ እስከ ፍጻሜ ለሚሳተፉ ክለቦች እንደተሳትፏቸው መጠን ገቢ ያከፋፍላል፡፡
በዘንድሮው የመጀመሪያ ምዕራፍ የቻምፒዮንስ ሊጉ ውድድር 36 ክለቦች በአንድ ምድብ ኾነው ተሳትፈዋል፡፡ስምንት ክለቦች በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፉ ሲቀላቀሉ 16 ክለቦች ደግሞ ቀሪ ስምንት የጥሎ ማለፍ ዙር ቦታዎችን ለማግኜት ወደ ደርሶ መልስ ጨዋታዎች አምርተዋል፡፡
የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ለ36ቱ የመጀመሪያው ዙር ተሳታፊ ክለቦች የሚደርሳቸውን የገቢ መጠን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ሁሉም ክለቦች በትንሹ 18 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ (16 ነጥብ 1 ሚሊዮን ፓውንድ) አግኝተዋል፡፡
በቀዳሚነት ከፍተኛውን ክፍያ ያገኜው ባየር ሙኒክ ኾኗል፡፡ መጀመሪያውን ምዕራፍ ውድድር ሁለተኛ ኾኖ ያጠናቀቀው የጀርመኑ ክለብ 100 ሚሊዮን ዩሮ ደርሶታል፡፡
አንድም ጊዜ ሳይሸነፍ ስምንቱንም ጨዋታዎች አሸንፎ አንደኛ ኾኖ የጨረሰው ክለብ የእንግሊዙ አርሰናል ነበር፡፡ ኾኖም ከሀገሩ ክለቦች ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ያነሰ ተከፋይ ነው የኾነው፡፡
አርሰናል 96 ሚሊዮን ዩሮ ሲያገኝ ሦሥተኛ ኾኖ የጨረሰው ሊቨርፑል እና ስምንተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ማንቸስተር ሲቲ እኩል 97 ሚሊዮን ዩሮ ደርሷቸዋል፡፡
በማኅበሩ የገቢ ድርሻ ስሌት መሠረት ክለቦች በመጀመሪያው ምዕራፍ ውድድር ያስመዘገቡት ድል እና አቻ ውጤት እንዲሁም ይዘው የጨረሱት ደረጃ ከአጠቃላይ የገቢ ክፍፍል መጠን 37 ነጥብ 5 በመቶውን ይይዛል፡፡
ኾኖም ቀሪውን እና ከፍ ያለውን ድርሻ የሚይዘው ክለቦቹ ባለፉት 10 ዓመታት በቻምፒዮንስ ሊጉ መድረክ የነበራቸው ተሳትፎ እና ያስመዘገቡት ውጤታማነት በመኾኑ የሲቲ እና ሊቨርፑል ድርሻ ከዘንድሮው ምርጥ ቡድን አርሰናል ከፍ ማለቱ ተመላክቷል፡፡
ቀሪዎቹ የእንግሊዝ ክለቦች ቸልሲ 92 ሚሊዮን ዩሮ፣ ቶተነሀም 84 ሚሊዮን ዩሮ፣ ኒውካስል ዩናይትድ 54 ሚሊዮን ዩሮ ደርሷቸዋል፡፡
በዘንድሮው ውድድር ከጥሎ ማለፉ ዙር እስከ ፍጻሜው የሚሳተፉ ክለቦች ቀጣይ ገቢ እንደሚኖራቸው የኢንዲፔንደንት መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



