በጥር የተጫዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ወጭ ያደረጉት እነማን ይኾኑ?

0
37

 

ባሕርዳር፡ ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማንቸስተር ሲቲ ለፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ ከአርሰናል ጋር የሚያደርገውን ፉክክር ለማጠናከር በዚህ የዝውውር መስኮት ትልልቅ ዝውውሮችን አከናውኗል።

ጥር 1/2018 ዓ.ም አጥቂውን ሴሜንዮን ከቦርንመዝ በ64 ሚሊዮን ፓውንድ ያስፈረሙ ሲኾን ተከላካዩን ማርክ ጉሄን ደግሞ ጥር 8/2018 ዓ.ም ከክሪስታል ፓላስ በ20 ሚሊዮን ፓውንድ ተቀላቅሏቸዋል።

የቀድሞዋ የእንግሊዝ እና የማንቸስተር ሲቲ ተከላካይ ስቴፍ ሆውተን ለቢቢሲ ሬዲዮ5 ላይቭ እንደተናገረው “አሁን ያለው ሁኔታ ማንቸስተር ሲቲ አርሰናልን እያሳደደ ያለበት ቢኾንም የነጥብ ልዩነቱ ግን እየሰፋ የመጣበት በመኾኑ ዝግጁ የኾኑ እና የፕሪምየር ሊጉን ጠንካራ ፉክክር የሚያውቁ ተጫዋቾች ያስፈልጋሉ ነው ያለው።

“ማርክ ጉሄን እና ሴሜንዮን ማስፈረሙ ከክለቡ በኩል ብልህነት የተሞላበት ርምጃ እንዳለ የሚያሳይ ነው” ብሏል።

ክሪስታል ፓላስ በመዝጊያ ቀኑ ስትራንድ ላርሰንን ማስፈረሙን ተከትሎ በክረምቱ መስኮት በአጠቃላይ 83 ሚሊዮን ፓውንድ ወጭ አድርጓል።

ይህም ብሬናን ጆንሰንን ከቶተንሃም በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ማስፈረማቸውን ይጨምራል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አስቶን ቪላ አጥቂው ታሚ አብርሃምን ከቤሺክታሽ ለማዛወር 18 ነጥብ 25 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም የክንፍ ተጫዋቹ አሊሰንን ከግሬሚዮ ለማስፈረም 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን ፓውንድ አውጥቷል።

የሊጉ መሪ አርሰናል በክረምቱ መስኮት ምንም አይነት ዝውውር ያላደረገ ሲኾን እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራት እስከ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቼልሲ እና ሊቨርፑልም ዝምታን መርጠዋል።

ማንቸስተር ሲቲ ለዋንጫ ፉክክር ቡድኑን ሲያጠናክር በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኘው ዌስትሃም ደግሞ ከሊጉ ላለመውረድ ከፍተኛ ወጭ አድርጓል።

በወራጅ ቀጠናው ደረጃ ላይ የሚገኙት መዶሻዎቹ ብራዚላዊውን አጥቂ ፓብሎ ፌሊፔን ከፖርቹጋሉ ጊል ቪሴንቴ በ21 ነጥብ 8 ሚሊዮን ፓውንድ እንዲሁም አጥቂውን ታቲ ካስቴላኖስን ከላዚዮ በ25 ሚሊዮን ፓውንድ ገደማ አስፈርመዋል።

14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቶትንሃም አጥቂውን ኮኖር ጋላገርን ከአትሌቲኮ ማድሪድ በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያስፈርም ቦርንመዝ ደግሞ ከሴሜንዮ ሽያጭ ካገኘው ገንዘብ ላይ ወጣቱን አጥቂ ራያንን ከቫስኮ ዳ ጋማ እንዲሁም የሃንጋሪውን አማካይ አሌክስ ቶትን ከፈርንክቫሮስ ለማስፈረም ተጠቅሞበታል። ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

በቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here