ባሕር ዳር፡ ጥር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ሊግ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ አርሰናል እና ቼልሲ ይጫወታሉ።
ቼልሲ ለዘጠነኛ ጊዜ አርሰናል ደግሞ ለ11ኛ ጊዜ ለሊግ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ለመድረስ ይጫወታሉ። ጨዋታው በኤምሬትስ ስታዲየም ምሽት 5:00 ይካሄዳል።
አርሰናል ከሁለት ሳምንት በፊት በስታምፎርድ ብሪጅ የነበረውን የመጀመርያ ዙር ጨዋታ 3ለ2 ማሸነፉ ይታወሳል።
አርሰናል ዛሬ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ከሚያደርገው ጨዋታ ነጥብ መጋራት ብቻ በቀጥታ ለፍጻሜ ያደርሰዋል፡፡
አሠልጣኝ ሚካኤል አርቴታ በጨዋታው ለማሸነፍ አቅደን ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።
ለአርሰናል ሚካኤል ሜሪኖ በጉዳት እንደማይሰለፍ ታውቋል።
ቼልሲ በሊያም ሮሰኒየርን መሠልጠን ከጀመረ ወዲህ ከፍተኛ መነቃቃት አሳይቷል።
ለአብነት ከሰሞኑ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ጣልያን አምርቶ ናፖሊን ማሸነፉ የጥንካሬው ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ሊያም ሮሰኒየር “ኤምሬትስ ሌላ ሀገር ያለ ሜዳ አይደለም። በርከት ያሉ ተጫዋቾች ቢጎዱብንም እነርሱን የሚተኩ ተጫዋቾች አሉን፤ ጥሩ ተጫውተን ከእነርሱ (አርሰናል) የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅማችንን አሟጠን እንጫወታለን” ብለዋል።
ለቼልሲ ዛሬ ጄሚ ጊተንስ፣ ሮሚዮ ላቪያ፣ ሌቪ ኮልዊል፣ ቶሲን አዳራባዮ እና ዳሪዮ ኢሱጎ የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።
አርሰናል የፕሪምየር ሊጉን እና የአውሮፖ ሻምፒዮንስ ሊግን መምራቱ የቡድኑን ጥንካሬ ያሳያል።
ቼልሲ ደግሞ ቀደም ሲል ከነበረበት ድባቴ ተነቃቅቶ ወደ አሸናፊነት ሥነ ልቦና ተመልሷል። በመኾኑም ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ጠንካራ፣ አጓጊ እና ውብ ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል ዴይሊ ሜይል አስነብቧል።
የሊግ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ በግዙፉ የዌይምብሌ ስታዲየም የሚደረግ ይኾናል። ለዚህ ፍጻሜ ጨዋታ የሚበቃው የአርሰናል እና የቼልሲ አሸናፊ ከማንቸስተር ሲቲ እና ኒውካስትል ዩናይትድ አሸናፊ ይኾናል፡፡
ዛሬ ምሽት 5:00 የእግር ኳስ አፍቃሪው ዐይን ሁሉ ኤምሬትስ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ። አርሰናል ወይስ ቼልሲ?
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



