የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የዛሬ ወሳኝ መርሐ ግብሮች

0
41
ባሕር ዳር: ጥር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ቀን 11:00 ላይ አስቶንቪላ ከብሬንትፎርድ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ ከፉልሃም እንዲሁም ምሽት 1:30 ማንቸስተር ሲቲ ከቶትንሃም የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አጓጊም የደረጃ ለውጥም የሚያስከትሉ ናቸው።
አስቶንቪላ ከ23 ጨዋታዎች እንደ ማንቸስተር ሲቲ ሁሉ 46 ነጥብ በመያዝ ግን በግብ ክፍያ ተበልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው።
የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የማንቸስተር ሲቲ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ የሁለተኛ ደረጃን እንዲቆናጠጥ ያደርገዋል።
ተጋጣሚው ብሬንትፎርድ ደግሞ በ33 ነጥብ ደረጃው ዘጠነኛ ነው። ጨዋታውን ካሸነፈ ደረጃውን የሚያሻሽል ይኾናል። በተመሳሳይ ቀን 11:00 ላይ ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ ከፉልሃም ጋር ይጫወታሉ።
ቀያይ ሰይጣኖቹ ከ23 ጨዋታዎች በ38 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ማንቸስተር ዩናይትድ ጨዋታውን በማሸነፍ ሊቨርፑልን እና ቼልሲን በመብለጥ ወደ አራተኛ ከፍ ስለሚያደርገው ጨዋታው የሞት ሽረት ይኾናል ተብሎ ተጠብቋል።
ተጋጣሚው ፉልሃም በ34 ነጥብ ሰባተኛ ነው። ቡድኑ ማንቸስተር ዩናይትድን ቢያሸንፍ ከታች ያሉ ቡድኖች ደረጃውን እንዳይነቀንቁት ያደርገዋል እንጅ ወደ ላይ ግን አያሳድገውም።
በተመሳሳይቀን 11:00 ላይ ኖቲንግሃም ፎረስት ከክሪስታል ፓላስ ይጫወታሉ።
በ25 ነጥብ 17ኛ ላይ ኾኖ ወራጅ ቀጣናው አፋፍ የተቀመጠው ኖቲንግሃም ፎሬስት ከስጋት ለመላቀቅ በ28 ነጥብ 15ኛ ላይ ያለው ክሪስታል ፖላስም ተንሸራትቶ ወደ ወራጅ ቀጣናው ላለመግባት ከፍተኛ ፉክክር ያደርጋሉ።
ሌላው አጓጊ እና ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 1:30 ላይ ማንቸስተር ሲቲ ከቶትንሃም የሚያደርጉት ነው።
ዜጎቹ ከ23 ጨዋታዎች 46 ነጥብ በመሠብሠብ የቅርብ ተፎካካሪውን አስቶንቪላን በግብ ክፍያ ብቻ በልጠው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ዛሬ ካሸነፉ ከሊጉ መሪ አርሰናል ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት አጥብበው ባሉበት ሁለተኛ ደረጃ መርጋት ያስችላቸዋል።
ለማንቸስተር ሲቲ አይደለም መሸነፍ አቻ መውጣት ከደረጃቸው ሸተት ስለሚያደርጋቸው ብርቱ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ነው የሚጠበቀው።
ተጋጣሚው ቶትንሃም ካሸነፈ አሁን ያለበትን 14ኛ ደረጃ አስከብሮ እንዲቆይ ይረደዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here