ባሕር ዳር: ጥር 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዛሬ ምሽት 5:00 በተለያዩ ከተሞች ከሚደረጉ 18 ጨዋታዎች መካከል ቼልሲ እና ናፖሊ በዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ሆኗል።
በሊያም ሮሴኒየር የሚሠለጥነው ቼልሲ ከሰባት ጨዋታዎች 13 ነጥብ በመያዝ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ቡድኑ በቀጥታ ወደ ጥሎ ማለፍ ለመግባት ዛሬ ናፖሊን ማሸነፍ ይኖርበታል። ለዚህም የቡድኑ እንደ 12ኛ ተጫዋች የሚቆጠሩ 2 ሺህ 500 የሚጠጉ ደጋፊዎች የስታዲየም መግቢያ ትኬት መያዛቸው ተረጋግጧል፡፡
ናፖሊ በበኩሉ ከሰባት ጨዋታዎች ስምንት ነጥብ ብቻ አስመዝግቧል፡፡ ደረጃው ደግሞ 25ኛ ነው፡፡ ቡድኑ ቼልሲን ድል ካደረገ በእርስ በእርስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ መድረስ ያስችለዋል፡፡ የናፖሊ ደጋፊዎችም በተለያዩ መንገዶች ቡድናቸውን ከማበረታት ባለፈ የቼልሲ ቡድንን በሥነ ልቦና ለማሸነፍ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
የጣልያን ፖሊስ የጨዋታውን ክብደት አስታኮም ባወጣው መግለጫ የቼልሲ ቡድን ደጋፊዎቸ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
ደጋፊዎች በከተማዋ እንዳይዘዋወሩ እና የቼልሲ ደጋፊ መኾናቸውን የሚጠቁሙ ቀለሞችን እና ዓርማዎችን ከመልበስ እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ከጨዋታው በፊት በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል ግጭት በመከሰቱ ሁለት የቼልሲ ደጋፊዎች ተጎድተው ለሕክምና ሆስፒታል መግባታቸውን ፖሊሲ ጨምሮ ገልጿል፡፡
የቼልሲ ቡድንም ባወጣው መግለጫ ደጋፊዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል፡፡ ”ይህ የእግር ኳስ ጨዋታ እንጅ ጦርነት አይደለም” ሲልም የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች ወደ ቀልባቸው እንዲመለሱ አሳስቧል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



