ባሕር ዳር: ጥር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ23ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ተጠባቂ ከነበሩት ጨዋታዎች መካካል ማንቸስተር ዩናይትድ አርሰናልን 3ለ2 ያሸነፈበት መርሐ ግብር ይገኝበታል፡፡
በዚህ ጨዋታ ድንቅ ግብ ያስቆጠረው ፓትሪክ ዶርጉ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት የጡንቻ መሸማቀቅ ጉዳት ገጥሞታል።
ዘ አትሌቲክ ባስነበበው ጽሑፍም ለ10 ሳምንታት ከሜዳ ሊርቅ እንደሚችል አትቷል፡፡
ዶርጉ በማይክል ካሪክ ስር በአዲስ ሚና ድንቅ እንቅስቃሴን እያሳየ ነው። በሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ግብም አስቆጥሯል።
በማይክል ካሪክ የተሰጠው ልዩ ሚና ለተጫዋቹ የቅርብ ጊዜ መሻሻልም ተጠቃሽ ነው። ከመከላከል ይልቅ ከሜዳው አጋማሽ ከፍ ብሎ ወደ ማጥቃቱ እንዲያዘነብል በሚያደርገው የአሠልጣኙ አሰላለፍ ዶርጉ ውጤታማ ሆኗል።
በዚህ የውድድር ዓመት ዶርጉ 22 ጨዋታዎች ተሰልፎ ሦስት ግቦችን ሲያስመዘግብ ሦስት ኳሶችን ደግሞ አመቻችቷል፡፡
ዶርጉ አሁን በገጠመው ጉዳት ምክንያት ስምንት ጨዋታዎች የሚያመልጡት ይኾናል፡፡
በሐናማርያም መስፍን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



