ባሕር ዳር፡ ጥር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ማንቸስተር ዩናይትድ በእንግሊዝ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የከበረ ዝናና የሚያስቀና ታሪክ ያለው ክለብ ነው።
ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያገኘ ሁሉ መረቡን የሚደፍረው እና የውጤት እጦት የሚያደፍንድፈው ክለብ ሆኗል። የክለቡ ደጋፊዎችም በሚወዱት ክለብ ውጤት ማጣት አንገታቸውን ደፍተው ሰንብተዋል።
የዩናይትድን ማንሰራራት እና የሊጉን የፉክክር መንፈስ እንዲመለስ ከደጋፊ እስከ የክለቡ የበላይ አለቆች ብዙ ባዝነዋል።
ቡድኑን ይቀይራሉ የተባሉ አሠልጣኞችም መጥተዋል፣ ሄደዋልም። በሰር አሌክስ ፈርጉሰን ዘመን ለተጋጣሚዎች ምጥ የነበረው ክለብ ተራ ሆኖ ማንም የሚፈራ ሆኗል።
አሁን ዩናይትድ በዝምተኛው የቀድሞ ኮከብ ካሪክ እጅ ይገኛል። ማይክል ካሪክ በተጨዋችነት ዘመን የዩናይትድ ባለውለታ ነው።
ካሪክ እንደ ፈረንጆቹ ከ2006 እስከ 2018 ድረስ ለማንቸስተር ዩናይትድ የተጫወተ ድንቅ አማካይ ነበር። በሜዳ ላይ ባለው ከፍተኛ የጨዋታ የማንበብ ችሎታ፤ ኳስን የማድረስ ጥበብ ድንቅ እንደነበርም ይነገርለታል።
ካሪክ ከክለቡ ጋር አምስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎችን እና አንድ ሻምፒዮንስ ሊግን ጨምሮ በርካታ ድሎችን አሳክቷል።
ከተጨዋችነት ዘመኑ ወደ አሠልጣኝነት ምዕራፍ ሲሸጋገርም ረዳት አሠልጣኝ በመኾን ነበር የጀመረው። በረዳት አሠልጣኝነት ዘመኑም በኦሌጉነር ሶልሻየር እና በሆሴ ሞሪንዮ ስር ረዳት አሠልጣኝ ኾኖ ሠርቷል።
ይህም የቡድኑን ውስጣዊ አወቃቀር እና ተጨዋቾቹን በሚገባ እንዲያውቅ ረድቶታል።
አሠልጣኝ ሶልሻየር ሲሰናበትም ቡድኑን ለጥቂት ጨዋታዎች መርቶ ሳይሸነፍ ለአሠልጣኝ ራልፍ ራኝክ አስረክቧል። ያኔም ቡድኑን ከሽንፈት አዙሪት በማውጣት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
አሠልጣኝ ካሪክ እንደ አሠልጣኝ የሚከተላቸው ልዩ የአሠለጣጠን ፍልስፍና እንዳለው ነው የሚነገረው።
አሠልጣኙ ቡድኑ በጭንቀት ውስጥ በሚኾንበት ጊዜ ተጫዋቾች በራስ መተማመን እንዲኖራቸው በማድረግ የተካነም እንደኾነም ከሰሞኑ በቀድሞ ትልልቅ ተጫዋቾች እየተመሰከረለት ነው።
በመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ግብ አለማስተናገድ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው አሠልጣኙ ከዚያም በፍጥነት ወደ ማጥቃት መሸጋገርን ተግባራዊ ማድረግ የካሪክ ፍልስፍና ነው።
በራስ መተማመናቸው የወረደ ተጨዋቾችን ቀርቦ በማነጋገር ወደ ብቃታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግበት መንገድ ካሪክን እያስወደሰው ነው።
የሠራው ለጥቂት ጊዜ፣ ይበልጥ ለማመስገንም ጊዜው አጭር ቢሆንም በኦልድትራፎርድ አሁን ፈገግታ እየታየ ነው።
ለዚህ ደግሞ ዝሞተኛው ካሪክ በፈጠረው ተነሳሽነት ሲቲ እና አርሰናልን በማሸነፍ የገናናውን ክለብ ታማኞች አንገት ቀና አድርጓል።
ይህን ተከትሎ ካሪክ አድናቆት እየጎረፈለት ነው።
ኦልድትራፎርድ ትክክለኛውን ሰው አግኝቶ ይሆን? እርስዎስ ምን ይላሉ?
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



