ከሙቦላዲንጋ ምን እንማር?

0
43
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2018ዓ.ም (አሚኮ) ጉሮሮው እስኪዘጋ በመጮህ እና ክንዶቹ እስኪዝሉ በመወራጨት አልደገፈም – እርጋታ፣ ሰላማዊነት፣ ጽናት እና አስታዋሽነትን መረጠ እንጂ፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት የብሔራዊ ቡድኑ ደጋፊ ኾኖም ተመዝግቧል፡፡
ሞሮኮ ባስተናገደችው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ክስተት ኾኖ ሰንብቷል፡፡ ሀገሩ በአልጀሪያ ተሸንፋ ከውድድሩ ውጭ ብትኾንም ባሳየው የተለየ ድጋፍ መነጋገሪያ ኾኗል፡፡
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ብሔራዊ ቡድን ደጋፊ የ49 ዓመቱ ማይክል ኩካ ሙቦላዲንጋ የሀገሩ የባንዲራ ቀለማት ያላቸው ልብሶችን በመልበስ፣ በከፍታ ቦታ ላይ ቆሞ ቀኝ እጁን ወደፊት ከፍ አድርጎ በመዘርጋት ሙሉ 90 ደቂቃውን ሲደግፍ ሰንብቷል፡፡
ለሀገሩ የቀድሞ መሪ እና የአፍሪካ አንድነት አቀንቃኝ ፓትሪስ ሉሙምባ በኪንሻሳ የቆመላቸውን ሐውልት በመምስል ነበር የዘከራቸው፡፡
ሀገሩ ኮንኮ በአልጀሪያ በተሸነፈችበት ጨዋታ የአልጀሪያ ተጫዋች ጎል አስቆጥሮ ቢሳለቅበትም ሙቦላዲንጋ እንባውን ከፊቱ ላይ ከመጥረግ በስተቀር ያሳየው ምላሽ አልነበረም ብሏል አልጀዚራ በዘገባው፡፡ ይህ የበርካታ የስፖርት ቤተሰብን ልብ የነካ እንደነበር እየተዘገበ ነው፡፡
ድርጊቶቹ ማስታወስ፣ ማክበር እና አንድነት ላይ የተመሠረተ የግል ፍልስፍናውን ያንጸባርቃሉ የተባለለት ምቦላዲንጋ የተረጋጋ፣ ቁርጠኛ እና ስለድርጊቱ አስፈላጊነት አሳቢ መኾኑም ተመስክሮለታል፡፡
የ2025ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ሕይወቱን እንደቀየረው ያስነበበው ደግሞ አፍሪካ ሶከር ነው፡፡ ለሥራው ቤትና መኪና መሸለሙን በመጥቀስም በእውነት እና በጽናት ላይ የተመሠረተ መልካም ሥራ የማታ ማታ ጠቃሚ መኾኑን አስነብቧል፡፡ ለሀገሩ የስፖርት ብራንድ አምባሳደርነትም ተሾሟል፡፡
ሌሎች አድናቆቶች እና ክብሮችም እየተሰጡት ነው፡፡ የሀገሪቱ ስፖርት ሚኒስትር ዲድየር ቡዲምቡ ብሔራዊ አንድነትን፣ በኮንጎ ሕዝብ መካከል ሰላምን እና አብሮ መኖርን በስፖርት መስበክ እንደሚቻል ማሳየቱን መስክረውለታል፡፡
በውድድሩ ተገኝቶ በአይረሴ ትዕይንቱ ለሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ድጋፍ ከማድረጉም በላይ በስፖርት የጨዋነት፣ የትዕግሥት እና የሰላማዊነትን አስፈላጊነት አስተምሮበታል፡፡
200 ቋንቋዎች በሚነገሩባት፣ የብሔር ግጭት፣ የአማጽያን እንቅስቃሴ እና የጎረቤት ሀገራት ጣልቃ ገብነት የታሪኳ አካል በኾኑት ኮንጎ ማይክል ኩካ ሙቦላዲንጋም የተወለደበት ብሔር እና የሚደግፈው ፖለቲካ አስተሳሰብ የለም ተብሎ አይታሰብም፡፡
ሙባላዲንጋ ግን የስፖርት መድረኩን ብሔሩን ለማግዘፍ፣ ቋንቋውን ለማስተዋወቅ፣ የፖለቲካ አቋሙን ለመስበክ ብሎም ጠላቶቼ የሚላቸውን ለመዝለፍ አልተጠቀመበትም፡፡
ይልቁንም የኮንጎአውያን ቀደምት ብሔራዊ ኩራት እና የነጻነት ታጋይ የፓትሪስ ሉሙምባን ሐውልት መስሎ በመቆም ስሜቱን ሲያጋራ ሰንብቷል፡፡
በከፍታ ቦታ ላይ በመቆም፣ ያለምንም እንቅስቃሴ እና ንግግር፣ ስሜትን ተቆጣጥሮ 90 ደቂቃ በመቆም የሀገርን ብሎም የአሕጉርን የሰላም፣ የነጻነት እና የጽናት ተምሳሌትነት ማሳየት ከጥሩ ስብዕናም በተጨማሪ መታደል ነው፡፡
ተጫዋች ጥፋት ሠራብን፣ ዳኛ አዳላብን ወይም ተሴረብን ብለው ከስፖርታዊ ሥነ ምግባር ውጭ ለሚጫዎቱ እና ለሚደግፉም አስተማሪ ነው፡፡
ስፖርትን በብሔር ለሚተረጉሙ፣ ሲሸነፉ ተጠያቂ ሰው እና ብሔር ለሚፈልጉ ሲያሸንፉም ባልተገባ ስሜት ሌሎቹን ለሚተነኩሱ እና ሀገር ወክለው ተወዳድረው የሰፈር ሰንደቅ ዓላማ ለሚያውለበልቡ የስፖርት ቤተሰቦች ሁነኛ መልዕክት አለው፡፡
ስፖርትን፣ ስፖርተኛነትን እና ደጋፊነትን ከማይክል ኩካ ሙቦላዲንጋ መማር ይገባል፡፡ ለቀደምቶቻችን አስተዋጽኦ ዋጋ በመስጠት የምናከብርበት፣ ብሔራዊ አንድነትን የምንሰብክበት፣ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ከፍ የምናደርግበት መኾን አለበት፡፡
ከቤልጅየም ቅኝ ግዛት ነጻነት ቀጥሎ በጠቅላይ ሚንስትርነት ተመርጠው ሀገራቸውን የመሩት ፓትሪስ ሉሙምባ ለነጻነት ባደረጉት ትግል እና መስዋዕትነት የአፍሪካ ኩራት መኾናቸው ይታወቃል፡፡
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here