ባሕር ዳር፡ ጥር 17/2018ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
በሊጉ 16ኛ ሳምንት ከሀድያ ሆሳዕና የነበረበትን ጨዋታ ያራዘመው ፋሲል ከነማ አንድ ጨዋታ እየቀረው በ26 ነጥብ እና በአምስት የግብ ክፍያ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ፋሲል ከነማ ዛሬ ከአርባምንጭ ከተማ ያለበትን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ደረጃውን ያሻሽላል።
በሌላ በኩል ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ በ8 ነጥብ የሊጉ ግርጌ ላይ የተቀመጠ ክለብ ነው። ክለቡ በባለፈው 16ኛ ሳምንት ጨዋታ ከምድረገነት ሽረ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 1ለ0 ተሸንፏል። ጨዋታውም በአዲስ አበባ ስታዲየም 10፡00 ይካሄዳል።
በሌላ የሊጉ ጨዋታ ባሕር ዳር ከተማ ከሀዋሳ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ምሽት 12:ዐዐ ላይ በአዳማ ሳይንስ ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል። ባሕር ዳር ከተማ በሊጉ 21 ነጥብ ሠብሥቦ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በ16ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከወላይታ ዲቻ ያለ ግብ የተለያየው ክለቡ ዛሬ የሚያደርገውን ጨዋታ በማሸነፍ ደረጃውን ለማሻሻል ነው የሚጫወተው።
ተጋጣሚው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በሊጉ 28 ነጥብ ሠብሥቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። በ16ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከነገሌ አርሲ ጋር የተጫወተው ክለቡ 2ለ0 መርታቱ ይታወሳል። ሀዋሳ ከተማ ዛሬ በሚያደርገው ጨዋታ ለባሕር ዳር ከተማ ፈተና ሊኾን እንደሚችል ነው የሚጠበቀው።
በሊጉ ዛሬ ሌሎች ሁለት ጨዋታዎችም ሲካሄዱ ሀድያ ሆሳዕና ከውልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ቀን 7፡00 ላይ እና አዳማ ከተማ ከመቀለ 70 እንደርታ ቀን 9፡00 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለ



