በታዳጊዎች ላይ መሥራት እየተቀዛቀዘ የመጣውን የእግር ኳስ ዘርፍ ያነቃቃል።

0
52

 

ደብረ ታቦር: ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን በፎገራ ወረዳ እና በወረታ ከተማ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ተተኪ የብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ ተጫዋቾች ምልመላ ላይ ትኩረት ያደረገ ውድድር እየተካሄደ ይገኛል።

ውድድሩ ላይ ከ13 ወረዳዎች የተውጣጡ ታዳጊ ልጆች እየተሳተፉም ነው። ከፎገራ ወረዳ እና ከላይ ጋይንት ወረዳ የመጡ የምልመላው ተሳታፊ ታዳጊ ፍቅር አስቻለው እና በረከት ሃይማኖት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተተኪ ለመኾን በሚደረገው ውድድር ውጤት ለማምጣት በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል

ታዳጊዎች ይህን ዕድል በማግኘታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸው ወደፊት ሀገራቸውን እና ራሳቸውን በእግር ኳስ ጨዋታ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሠሩም አብራርተዋል።

የሊቦ ከምከም ወረዳ የሥልጠና እና ውድድር ባለሙያ ምህረቱ ልደቱ ለውድድሩ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሥራታቸውን ተናግረዋል።

ውድድሩ አቅም እና ችሎታ ላላቸው ታዳጊ ሕጻናት ተስፋ የሚሰጥ ለኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለውን የእግር ኳስ መቀዛቀዝ ችግር በመፍታት በተሻለ ደረጃ እንዲያድግ የሚያደርግ መኾኑንም አመላክተዋል።

ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 15 ዓመት ያሉ ታዳጊዎች ተሳታፊ የኾኑበት የደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር ተተኪ የብሔራዊ ቡድን የእግር ኳስ ተጫዋቾች ምልመላ እየተካሄደ መኾኑን የተናገሩት የደቡብ ጎንደር ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ስሜነህ ደሳለኝ ናቸው ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በእግር ኳስ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳሉት ሀገራት የኢትዮጵያን እግር ኳስ የተሻለ ደረጃ ላይ ኾኖ ማየት ይፈልጋል ነው ያሉት።

የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሃሳብ አመንጭነት ክህሎት እና ብቃት ያላቸው ታዳጊዎች ኢትዮጵያን ወክለው እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here