ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የእንግሊዝ ሊግ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ቼልሲን ከአርሰናል በስታምፎርድ ብሪጅ ምሽት 5፡00 ላይ ያገናኛል።
ሁለቱ ቡድኖች እንደ አውሮፖ አቆጣጠር ከ1995 ወዲህ በ79 ጨዋታዎች ተገናኝተው አርሰናል በ29 ጨዋታዎች አሸንፏል።
ቼልሲ ደግሞ በ26 ጨዋታዎች ድል ነስቷል። ሁለቱ ቡድኖች በ24 ጨዋታዎች አቻ ነው የተለያዩት።
ቼልሲ እና አርሰናል በአራት የሊግ ካፕ ጨዋታዎች ተገናኝተው ቼልሲ በሁለቱ ሲያሸንፍ አርሰናል ያሸነፈው በአንድ ጨዋታ ነው።
አዲሱ የቼልሲ አሠልጣኝ ሊያም ሮሴኒር የተረከቡት ቡድን በፕሪሚየር ሊጉ ከ21 ጨዋታዎች በስድስት ጨዋታዎች ተሸንፎ፣ በሰባቱ አቻ ተለያይቶ 31 ነጥብ በመያዝ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አሠልጣኙ የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ስማቸውን በደማቅ ቀለም ለማጻፍ በእጅጉ ይረዳቸዋል ነው የተባለው።
ቼልሲ በደጋፊዎቹ ፊት እና በአዲስ አሠልጣኝ መቅረቡ የሥነ ልቦና የበላይነት ስለሚኖረው የማሸነፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው ሲል ዴይሊ ሜይል አስነብቧል።
ቼልሲ ሞይሰስ ካይሴዶ እና ሮሚዮ ላቪያን ሳያሰልፍ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ነው የተገለጸው።
ተጋጣሚው አርሰናል በሊጉ ካደረጋቸው 21 ጨዋታዎች የተሸነፈው በሁለት ጨዋታዎች ብቻ ነው። በ15 ጨዋታዎች አሸንፎ እና በአራቱ አቻ ተለያይቶ 49 ነጥብ በመሠብሠብ የሊጉ መሪ ነው።
መድፈኞቹ አንድ እጃቸውን ዋንጫው ላይ ያሳረፉ በመኾኑ በቼልሲ ሊፈተኑ ቢችልም አሸናፊ መኾናቸው ግን አይቀርም የሚሉ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም።
አርሰናል በዛሬው ጨዋታ ሪካርዶ ካላፊዮሪ፣ ፒዬሮ ሂንካፔ እና ሞስኴራን በጉዳት ምክንያት እንደማያሰልፍ እየተነገረ ነው።
ከቼልሲ እና አርሰናል በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ቡድን ከማንቸስተር ሲቲ እና ኒውካስትል ዩናይትድ ድምር ውጤት አሸናፊ ጋር ለዋንጫ የሚጫወት ይኾናል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



