የዋንጫ ጨዋታ ያህል ትኩረትን የሳበው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ።

0
45
ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሁለት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ አስተናጋጇ ሞሮኮ ከናይጀሪያ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ምሽት 5:00 ላይ ነው በስታዲ ንጉሥ ሙላይ አብደላህ ስታዲየም ሞሮኮ እና ናይጀሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት።
ናይጀሪያ በዚህ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ያደረገቻቸውን የምድብ ሦሥት ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፋለች። ሞሮኮ ግን ከሦሥቱ በሁለቱ አሸንፋ በአንዱ አቻ ነው የተለያየችው።
ሁለቱ ሀገራት በታሪክ በተገናኙባቸው 11 ጨዋታዎች ሞሮኮ በስድስቱ በማሸነፍ የበላይ ናት። ናይጀሪያ ያሸነፈችው በአምስቱ ነው። በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ናይጀሪያ እና ሞሮኮ ካላቸው ወቅታዊ አቋም እና ካሠባሠቡት ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች አንጻር ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ተጠብቋል።
ሞሮኮ በደጋፊዎቿ እና በሜዳዋ እንደመጫወቷ በተጫዋቾች ላይ ጫና ሊበዛባቸው ይችላልም እየተባለ ነው።
የሞሮኮው አሠልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉይ እንዳሉት በአዕምሮ፣ በአካል እና በቴክኒክ ዝግጁ ናቸው።
“በደጋፊዎቻችን ታግዘን የጋራ ግባችን የአፍሪካ ዋንጫን ማሸነፍ ነው “ብለዋል።
የናይጄሪያ አሠልጣኝ ኤሪክ ቼል “ሞሮኮ ብራሂም ዲያዝን የመሰሉ ጥሩ ተጫዋቾች ያሉት በጣም ጥሩ ቡድን ነው፤ ይሁን እና ለእያንዳንዱ ነገር በሚገባ ተዘጋጅተናል፤ ጨዋታውን እንደ ዋንጫ ቆጥረን ነው የምንጫወተው” ብለዋል።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here