ባሕር ዳር: ጥር 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በእንግሊዝ ሊግ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ኒውካስትል ዩናይትድ እና ማንቸስተር ሲቲ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ እና አጓጊ ኾኗል።
ጨዋታው በሴንት ጀምስ ፖርክ ስታዲየም ምሽት 5:00 ላይ ይደረጋል።
ያለፈው ዓመት የሊግ ካፕ አሸናፊው ኒውካስትል ዩናይትድ ድሉን ዘንድሮም ለማስቀጠል ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የኒውካስትል ዩናይትድ አሠልጣኝ ኤዲ ሃው “ማንቸስተር ሲቲ በጣም አስቸጋሪ ቡድን ነው። በመኾኑም በጨዋታው በተለየ ሁኔታ እንደሚፈትነን እንረዳለን። ነገር ግን እኛም ከእነርሱ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተን ተዘጋጅተናል። አሸንፈን ለፍጻሜ ለመድረስ እንጫወታለን ” ብለዋል።
ኒውካስትል ዳን በርን፣ ኢሚል ክረፍዝ፣ ፋቢያን ሸር እና ዊሊያም ኦሱላ የማያሰልፋቸው ተጫዋቾች ናቸው ተብሏል፡፡
ተጋጣሚው ማንቸስተር ሲቲ በሊጉ 43 ነጥብ በመሠብሠብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ጠንካራ ቡድን ነው። በሊጉ የሚያሳየውን ጥንካሬ በሊግ ካፑም እንደሚደግመው ይጠበቃል።
የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ጨዋታው ከባድ እንደሚኾን ተናግረዋል። የሚጫወቱት ግማሽ ፍጻሜውን ለማሸነፍ ብቻ ሳይኾን ዋንጫን ለመውሰድ እንደኾነም አንስተዋል።

በሲቲ በኩል ጆን ስቶንስ፣ ሩብን ዲያዝ፣ ሳቪኒኾ እና ቦብ ዛሬ የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው ተብሏል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከአሁን ቀደም በሦስት የሊግ ካፕ ጨዋታዎች ተገናኝተው ኒውካስትል ዩናይትድ በሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ የበላይ ነው።
ማንቸስተር ሲቲ ያሸነፈው በአንድ ጨዋታ ነው።
ከኒውካስትል ዩናይትድ እና ማንቸስተር ሲቲ አሸናፊው ቡድን ከአርሰናል እና ቼልሲ አሸናፊ ጋር ለዋንጫ የሚጫወት ይኾናል፡፡
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



