ሀገር የማስተዋወቅ ዓላማ ያለው እና “ከአንኮበር እስከ ሐረር በር” የሚል መሪ መልዕክት ያለው ውድድር በደብረ ብርሃን ተጀምሯል።

0
7
ጥር 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ብርሃን የደመቀችበት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የስፖርት ቱሪዝምን ለማጠናከር የተዘጋጀ መርሐ ግብር ነው።
“ከአንኮበር እስከ ሐረር በር” በሚል መሪ መልዕክት ሀገርን በሩጫ አማካኝነት እያስተዋወቀበት የሚገኘው የስድስተኛው ከተሞች ውድድር ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ተጀምሯል።
ከሕጻናት እስከ አዋቂዎች በስፋት በተሳተፉበት በዚህ ውድድር የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በአትሌቶች የውድድር ዘርፍ አሸናፊዎች ኾነዋል።
ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡ አሸናፊዎች እንደየቅደም ተከተላቸው የአስራ አምስት፣ የአስር እና የስምንት ሺህ ብር ተሸላሚዎች ኾነዋል።
ውድድሩን ያስጀመሩት የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ዝግጅቱ የከተማዋን ቱሪዝም እና ስፖርት የሚነቃቃ እንደኾነ ገልጸዋል።
ደብረ ብርሃን የበርካታ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ መዳረሻ መኾኗን ያነሱት አቶ በድሉ በተለይ በጥር ወቅት የተሻለ የቱሪዝም ፍሰት መኖሩን ጠቅሰዋል።
ዛሬ ላይ የተጀመረውን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ይበልጥ በማሳደግ እና በማስቀጠል ቱሪዝም የሚገኘውን ሀብት ለማሳደግ ከወዲሁ ጥረት እየተደረገ እንደኾነም ነው አቶ በድሉ የገለጹት።
ታሪኩ ነጋሽ በቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት ላለፉት 60 ዓመታት እና ከዚያ በላይ ለሚኾን ጊዜ የቱሪዝም እንቅስቃሴው በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ብቻ በማተኮሩ ተፈላጊውን ጥቅም ማግኘት አልተቻለም።
አሁን ላይ ግን ዘርፉ ያለውን እምቅ ሀብት መጠቀም እንዲቻል ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል አንዱ በማድረግ እንደ ሀገር በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል፡፡
ዛሬ የተጀመረው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መርሐ ግብርም ይህንን ይበልጥ ለማሳለጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅ ቡድን አባሏ ህሊና ንጉሤ እንዳሉት ደግሞ ስፖርቱ የቱሪዝም አንድ አካል እንዲኾን ከማድረግ በዘለለ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት፣ ስፖርቱን ለማነቃቃት እና የውድድር እድል ላላገኙ ስፖርተኞች እድሉን ለማመቻቸት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑን አብራርተዋል።
በየጊዜው የተዘጋጁ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መርሐ ግብሮች ለስፖርቱ እድገት ጉልህ አበርክቶ ማድረጋቸውንም ነግረውናል።
የ2018 ዓ.ም ‘ልወቅሽ ኢትዮጵያ ክላሲክስ‘ በቀጣይ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ በቆጂ፣ አርባ ምንጭ እና ሐረር ተመሳሳይ ውድድር የሚደረግባቸው መኾኑንም የመርሐ ግብሩ አዘጋጆች ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here