ባሕር ዳር: ጥር 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ሁለት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች በተለያዩ ሰዓታት መከናወን ይጀምራሉ።
ምሽት 1:00 ላይ ማሊ ከሴኔጋል በግራንዴ ዴ ታንገር ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሴኔጋል ከማሊ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2004 ወዲህ በሰባት ጨዋታዎች ተገናኝተው ማሊ በአምስቱ ስታሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል።
ሁለቱ ሀገራት በአንድ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታም ተገናኝተው አቻ መለያየታቸው ይታወሳል። የማሊ ቋሚ ተሰላፊዎች በታላላቅ የአውሮፓ፣ የእስያ እና የአፍሪካ ቡድኖች እንደ መጫወታቸው ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ናቸው።
የማሊው አሠልጣኝ ቶም ሴንትፊት ሴኔጋልን ለማሸነፍ ሁሉንም ነገር እናደርጋለን ነው ያሉት።
የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በሳዑዲው አል ናስር በሚጫወተው ሳዲዮ ማኔ ፊት አውራሪነት የሚመራ ቢኾንም ሁሉም ቋሚ ተሰላፊዎች ፕሮፌሽናል ናቸው።
ሴኔጋላዊው አሠልጣኝ ፓፔ ቲያው” ሴኔጋላውያን ዋንጫውን እያሰብን እንጫወታለን። የተጫዋቾቻችን ችሎታ እና ብቃትም አስተማማኝ ነው። ጥሩ ተጫውተን ለማሸነፍ ነው ዓላማችን”ብለዋል።
በሌላ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ምሽት 4:00 ላይ ካሜሩን ከአዘጋጇ ሞሮኮ በስታዲ ንግሥ ሙሊይ አብደላህ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች በሦስት የአፍሪካ ዋንጫ ተገናኝተው ካሜሩን በሁለቱ ድል ነስታለች።
በአንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
የሞሮኮ ቡድን በፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የተሞላ ነው። በተለይም ቡድኑ በእነ አሽራፍ ሀኪሚ፣ ብራሂም ዲያዝ እና ማዝራዊ ላይ ያሳደረው ተስፋ ከፍተኛ መኾኑ እየተነገረ ነው።
ተጋጣሚው ካሜሩን ዓለም አቀፍ ልምድን ባካበቱ ስመ ጥር ተጫዋቾችን ይዞ ነው ወደ ሜዳ የሚገባው።
ቡድኑን በማንቸስተር ዩናይትድ የሚጫወተው ብራያን ምቤሞ ላይ ትልቅ ተስፋ አድርጓል።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



